Get Mystery Box with random crypto!

ባለፀግነት ስትወለዱ ጀምሮ የተሰጣችሁ መብት ነው! ምንጭ፦ ንቃተ ህሊና (ኦሾ) ትርጉም ፦ አና | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ባለፀግነት ስትወለዱ ጀምሮ የተሰጣችሁ መብት ነው!

ምንጭ፦ ንቃተ ህሊና (ኦሾ)
ትርጉም ፦ አና ፍራንክ

ሕይወት ማለት በሁሉም ነገር መብዛት፣ መበልፀግ ነው። ህልውናን (ተፈጥሮን) ተመልከቱ። ድሃ ይመስላችኋል? ጥዑም መዓዛ ያላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አበቦች ተመልከቷቸው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ከዋክብት ተመልከቷቸው፤ የሰው ልጅ ሊቆጥራቸው እንኳን አልቻለም፣ ይቆጥራቸዋል ብዬም አላስብም። በአይናችሁ ብሌን ቢበዛ ሶስት ሺ ከዋክብትን ማየት ብትችሉ ነው፤ ይህ ደግሞ ምንም አይደለም። እነዚህ ከዋክብት እየሰፉ ነው። አንድ አበባ ፈክቶ ቅጠሎቹ እንደሚዘረጋጉ ዩኒቨርስም በከፍተኛ ፍጥነት እየሰፋ፣ እያበበ፣ እየተከፈተ ነው። ከዋክብቱ ከመሃል እየራቁ ነው። መሃሉ በትክክል የት እንደሚገኝ አናውቅም፥ አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው መላው ዩኒቨርስ በፍጥነት እየተንቀሳቀሰ፣ ህያው እየሆነ ነው።

ይህን አካባቢ ሊጎበኙ የሚመጡ ሰዎች ህይወት ምን እንደሆነ አያውቁም። እኒህ ሰዎች ህይወትን ፍፁም አልኖሩም። አዎ፣ ተወልደዋል፤ ነገር ግን ህያው ለመሆን መወለድ ብቻውን በቂ አይደለም። እየበሰበሱ እየኖርን ነው ይላሉ። ምንም ሳይኖሩ አንድ ቀን ይሞታሉ። በዓለም ዙሪያ እንዲህ አይነት ተዓምራት ይከሰታሉ፤ ሰዎች ሳይኖሩ ይሞታሉ. . . ፍፁም የማይቻል ነገር! ሆኖም ይህ ነገር ሁልጊዜ ይከሰታል። ብዙዎች ይህ ነገር የሚገባቸው ከሞት አፋፍ ሲደርሱ ነው፤ ከሞት በራፍ ላይ ቆመው አስገራሚ ነገር ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ህይወትን እንዳልኖርኳት አሁን ገባኝ» ይላሉ።

በዚህ ሁኔታ የምትኖሩ ከሆነ ለምንድነው የምትኖሩት? ለፍቅር፣ ለደስታ፣ ለፍስሃ. .. ካልሆነ ለምን ትኖራላችሁ? «ብልፅግና» ምንድነው? ብልፅግና ህይወትን የበለጠ አስደሳች፣ የበለጠ ተወዳጅ፣ የበለጠ ምቹ፣ የበለጠ የሚደላ ማድረግ ነው።

ታላቁን የሙዚቃ ዓለም የማያውቅ ሰው ድሃ ነው፤ ይህ የጐደለው ሰው ከህይወት ታላላቅ ምቾቶች አንዱን አጥቷል። በፒካሶ፣ በቫን ጉህ ስራ ያልተደሰተ ስለ ቀለማት ምንም አያውቅም፤ በፀሃይ ውጣትና ግባት ካልተደሰተ እንዴት በሊኦናርዶ ዳ ቪንቺ ስራ ሊደሰት ይችላል? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለቅፅበት እንኳን ቆም ብለው ፀሃይዋ ስትወጣ ስትገባ፣ ከሰማዩ ጀርባ ቀለሟን ስታፈስ ሳይመለከቱ ኖረው ይሞታሉ።

መኖር ማለት ህይወትን በምሉዕነት ማሳለፍ ነው - ሙዚቃውን፣ ግጥሙን፣ ስዕሉን፣ ቅርፃ ቅርፁን ማጣጣም። እኔ የድህነት አምላኪ አይደለሁም - የድሎት እንጂ። ህልውና ደግሞ የተረፈው፣ የተትረፈረፈው ነው። አንድ አበባ በቂ ሆኖ ሳለ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አበቦች ያብባሉ። ህልውና ምስጢር ሆኖባችሁ አያውቅም? የከዋክብት መብዛት ለምን አስፈለገ?

ይህን ጥያቄ ያቀረቡት እነዚህ ቂሎች የሚያምኑበትን ፈጣሪ ቢያገኙት «የከዋክብቱ መብዛት ለምን አስፈለገ? ይህ ሁሉ ምቾት ምንድነው? ጥቂት ነገሮች አይበቁም ነበር? ብዙ አዕዋፍ፣ እንስሳት ሰብአዊ ፍጡራን መኖራቸው ለምን አስፈለገ?» ብለው በጠየቁት ነበር።

ሳይንቲስቶች በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት ቢያንስ ሃምሳ ሺ የሚሆኑ ፕላኔቶች አሉ። ምን አይነት ቀለም፣ ምን አይነት ቅርፅ፣ ምን አይነት ውበት እንዳላቸው አናውቅም፡፡ አንድ ነገር እርግጥ ነው ህልውና የተትረፈረፈ መሆኑ። ሁሉም ነገር የምቾት ነው። ህልውና ድሃ አይደለም። ድህነትን የፈጠረው ሰው ነው።

መንደራችንን ለማየት እዚህ የሚመጡት ሰዎች እዚህ ሲመጡ በአዕምሯቸው አንድ ነገር ይዘው መሆን አለበት። ምናልባትም «ጋንዲ» የሚለውን ፊልም አይተው ይሆናል፤ ስለ ምስራቃውያን ምናኔም ሰምተው ይሆናል። እኔ መናኝ አይደለሁም። እኔ ያን ያህል ደደብ አይደለሁም። እኔ ማህተማ ጋንዲ አይደለሁም። እሱን አጥብቄ ነው የምቃወመው። በዓለም ላይ ለሚታየው ድህነት ተጠያቂዎቹ እንደ ማህተማ ጋንዲ ያሉ ሰዎች ናቸው።

አዎ በጋንዲ መንደር ውስጥ እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚጠይቅ አይኖርም። ወደዚያ መንደር ብትሄዱ ሃዘን ይሰማችኋል። የጋንዲ ልጅ ራምዳስ እኔን ለማግኘት በጣም ፈልጐ ስለነበር አንድ ቀን ጋበዘኝ። ወደዚያ የሄድኩት ጋንዲ ከሞተ በኋላ ነበር። በግቢው ውስጥ ሰላሳ፣ ሰላሳ አምስት ሰዎች አሉ፤ ሁሉም ከጋንዲ ጋር ነበር የሚኖሩት። እናም ራምዳስን «እነዚህን ሰዎች ለምን ታሰቃዮዋቸዋላችሁ? በድህነት፣ በተራ ኑሮ ስም እነዚህን ሰዎች ከህይወት አውጥታችኋቸዋል» አልኩት። የሚበሉት ነገር በሙሉ አይጣፍጥም። ህንድ ውስጥ አንድ ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ሊያስወግድ ከሚገቡት ነገሮች አንዱ ጣዕም ነው። ማር አምስት ታላላቅ መርሆች አሉት፡ አንዱ የጣዕም አልባነት መርህ ነዉ እነዚያ ታላላቅ የሚባሉት አምስት መርሆች እውነት፣ ሰላማዊነት፣ ንብረት አልባነት፣ አለመስረቅና ጣዕም አልባነት ናቸው።

@Zephilosophy
@Zephilosophy