✞ በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን :: ✞ ✞ ነሐሴ 26 ✞ +*" አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ "*+ =>እኒህ ጻድቅ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው:: "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው:: ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል:: +ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ : እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች:: በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ : ምጽዋትን ወዳጅ : ቡርክት ሴት ነበረች:: እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር:: +ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማሕጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች:: ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ 7 አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች:: +ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕጻን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ:: ይሕችን ጸሎት በሕጻን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር:: +የ5 ዓመት ሕጻን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል:: ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ:: ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:: የፈጣሪውን ስም ያቃለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል:: +ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ት/ቤት ገብተው : መጻሕፍትንም አጥንተው መንነዋል:: በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በሁዋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም:: *ባሕር ውስጥ ሰጥመው 500 ጊዜ ይሰግዳሉ:: *በየቀኑ 4ቱን ወንጌልና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያሉ:: (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው) *በ40 ቀናት : ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ:: *ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው:: *በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ:: (ካህን ናቸውና) *ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ : ክቡር ደሙን ይጠጣሉ:: *በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን : መከፋትን አላሳደሩም:: +በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር:: ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በሁዋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከተትሎ መጥቶ አላቸው:: "1.ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ: 2.ስለ ምናኔሕ: 3.ስለ ተባረከ ምንኩስናህ: 4.ስለ ንጹሕ ድንግልናህ: 5.ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ: 6.ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ: 7.ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን እሰጥሃለሁ::" +"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን : 500 የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ : በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ አማንየ! በርእስየ! ብዬሃለሁ" አላቸው:: +ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: በዝማሬም ወሰዷት:: =>አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን: ክብራቸውን: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን:: =>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና:: ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና:: ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ:: በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ:: የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል:: አንደበቱም ፍርድን ይናገራል:: የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው:: በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31) ✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞ 84 views Dawit , 15:05