2022-01-28 13:00:22
{ትላንት የጠየቃችሁኝን ጥያቄ እኔ ደሞ Tewodros Shewangizaw ጠይቄው ይህን መልስ ሰጥቶኛል ። ጥያቄያችሁ በቂ ምላሽ እንዳገኘ ተስፋ አደርጋለሁ }
ጥያቄ፦ ቴዲ " የአገራችን ደራሲዎች ለምን ደሃ ሆኑ ? በድርሰታቸውስ ውስጥ ለምን ድህነት ይገለፃል ?".አንተ ምን ትላለህ?
አጭሩ መልስ፦ ድርሰት ወፍራም እንጀራ አያበላም።
ረዥሙ መልስ፦ አብዛኛዎቹ ቀደምት የኢትዮጵያ ደራሲዎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች፣ ሚኒስትሮች ወዘተ ነበሩ። ከበደ ሚካኤል በሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የትምህርት ሚኒስትር ነበሩ። በአሉ ግርማ የደርግ ማስታወቂያ ሚኒስትር ዋና ፀሀፊ ነበር። መኮንን እንዳልካቸው ሚኒስትር ነበሩ። ልጃቸው እንዳልካቸው መኮንን የሚኒስትር ልጅ፣ ራሳቸውም በስማቸው በተሰየመው የእንዳልካቸው ካቢኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ሀዲስ አለማየሁ በተባበሩት መንግስታት፣ በእንግሊዝ እና እስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።
አፈወርቅ ገብረየሱስ ራሱ እንደ ሚኒስትር ሊቆጠሩ የሚችሉ፣ በሁለት ሃገሮች ጉዳይ ላይ በማማከር እጃቸውን ያስገቡ ሰው ነበሩ። ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንና ባህላዊ አለባበሳቸው በራሱ ግዝፈትና በሚመለከታቸው ሰው ላይ ጫና የሚያሳድር፣ ከላይ ካባ ከውስጥ ቀጭን ኩታ የማይለያቸው ነበሩ። ሀዲስ አለማየሁ በባለቤታቸው ክበበ―ፀሐይ ለተሰየመው ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ማሳደጊያ እንዲሆን 3000 ካሬ ሜትር ቤታቸውን የሰጡ ነበሩ።
ይህንን ሁሉ የዘበዘብኩት ያለ ምክንያት አይደለም። እነዚህ ሁሉም ከላይ የተጠቀሱት ደራሲዎች በመንግስት ከፍተኛው መዋቅር ውስጥ ሆነው ወፍራም እንጀራ የሚያበላ ዋና ስራ ነበራቸው። ድርሰት ዝንባሌያቸው እንጂ እንጀራ መጋገሪያቸው አልነበረም። ኑሯቸውም የተድላና የድሎት ነው። የገንዘብ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ሰዎች አልነበሩም። ለመፃፍ የሚሆን ግዜ ካጡ እንጂ የመፃህፍቶቻቸው መሸጥ አለመሸጥ የሚያስጨንቃቸው አልነበሩም። ገበታቸው ሙሉ ቤታቸው ምቹ ነበር። በአጭሩ ድርሰት መተዳደሪያቸው አልነበረም።
ድርሰት መተዳደሪያቸው የነበሩ ደራሲዎችስ?? ለዚህ አብይ ምሳሌ የሚሆነን ጋሽ ስብሐት ነው። ስብሐት እንኳን ሞልቶ ተርፎት የድሎት ኑሮ ሊኖር ይቅርና ከወር ወር የሚደርሰው በመከራ ነው። ይህንን ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ አጭር ታሪክ ልንገራችሁ፦
ተስፋዬ ገብረአብ ቀሽት የነበረውን እፎይታ መፅሄት በሚያዘጋጅበት ግዜ ስብሀት ገብረእግዚአብሔርን፣ ደምሴ ፅጌን፣ የሺጥላ ኮከብን ወዘተ ወዘተ አምደኛ አደረጋቸው። እነዚህ ጋዜጠኛዎችና ደራሲዎች በችሎታቸው የተመሰገኑ ሲሆኑ ከያሉበት በባትሪ ፈልጎ ያሰባሰባቸው ተስፋዬ ራሱ ነው። ታዲያ አንድ ቀን ጋሽ ስብሐት አለቃው ተስፋዬ ገብረአብ ጋር ይመጣና እንዲህ ይለዋል፦
"ያለፈውን ወር ደሞዝ ስለወሰድኩ ልጠይቅህ አልችልም። የሚቀጥለውን ወር ደሞዜንም ልጠይቅህ አልችልም። እሱንም ወስጄዋለሁ። ስለዚህ ለምን ታታሪ ሰራተኛ ብለህ አትሸልመኝም"
የተስፋዬ ገብረአብ ሳቅ ጆሮ አደንቋሪ እንደነበር አይጠረጠርም። ይህንን ታሪክ ለምን ለመንገር ፈለግኩ? በደራሲነት ችሎታ ስብሐትን የሚገዳደር እግር እስኪነቃ ቢፈለግ አይገኝም። ድርሰት የቁስ ሃብታም የሚያደርግ ቢሆን ኖሮ ስብሐት ቱጃር ይሆን ነበር።
ወደ መሰረታዊው ጉዳይ እንምጣ። እንደ ሃገር ማህበረሰባችን ለሃሳብ፣ ለጥበብ የሚሰጠው ቦታ የወረደ ነው። የማንበብ ባህል ደካማ ነው። ለ100 ሚሊየን ህዝብ አስር ሺህ ኮፒ መፃህፍት ተሽጦ ካለቀ እንደ ተአምር ይወራል። አንባቢ እንደ እብድ፣ ደራሲ እንደ ስራፈት የሚታይበት ሃገር ነው። የኢኮኖሚ ድህነት አለ፣ የአስተሳሰብ ድህነት አለ። የህትመት ዋጋ ውድ ነው። ወረቀት ይቀረጥበታል። መንግስት ደራሲዎችንና የንባብ ባህልን አያበረታታም። የደራሲዎች ሽልማት አያዘጋጅም። ቤተመፃህፍት በብዛት የሉም። የመፅሀፍት መደብሮች ጥቂት ናቸው። የነበሩትም እየተዘጉ ካፌና ምግብ ቤት ይከፈትባቸዋል። ከአእምሮው ይልቅ ለሆዱ የሚጨነቅ ማህበረሰብ እና ትውልድ ነው ያለን። ችግሩ ስር የሰደደና ዘርፈ ብዙ ነው። ታዲያ ደራሲዎች በየት በኩል ድሃ አይሁኑ?! በእርግጥ ድርሰት የንግድ መስክ አይደለም። ይሁን እንጂ ለሙሉግዜ ደራሲ ብቸኛ መተዳደሪያው ነው። ደራሲ እንደ ሁላችንም ሰው ነው። ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይለብሳል። ለዚህ ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል። ማጠቃለያው ድርሰት እዚህ ሃገር እንኳን ሙሉ፣ ግማሽ እንጀራ አያበላም ነው!
(ምስሉ ተረት ሰፈር ይገኝ የነበረው የጋሽ ስብሐት ቤት ነው። ይሄ ምስል የኢትዮጵያ ደራሲዎች ድህነትን ጠቅልሎ የሚገልፅ አንድ ፎቶ ነው)
448 views10:00