Get Mystery Box with random crypto!

ስዊፍት/SWIFT ምንድነው? __ ሰሞኑም አሜሪካ እና አጋር የአውሮፓ ሀገራት በዓለም የንግድ ታሪክ | #ቁርጥራጭ ሀሳቦች በየቲ

ስዊፍት/SWIFT ምንድነው?
__
ሰሞኑም አሜሪካ እና አጋር የአውሮፓ ሀገራት በዓለም የንግድ ታሪክ ከኢራን በመቀጠል የተወሰኑ የሩሲያ ባንኮች የስዊፍት ስርአትን እንዳይጠቀሙ አግዷል። ለመሆኑ ስዊፍት/SWIFT ምንድነው?

SWIFT የሚለው ቃል ምህጻረ-ቃል ሲሆን የሚወክለው Society of Worldwide Interbank Financial Telecommunications የሚለውን ነው። ይህ ስርአት በቤልጂየም ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1973 የተመሠረተ ተቋም ነው። የስዊፍት ስርአት ፋይናንስ ነክ መረጃዎች በፍጥነት፣ በአስተማማኝ ሁኔታ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በአለም ላይ በሚገኙ 200 ሀገራት ውስጥ ያሉ 11,000 ባንኮች እንዲላላኩ ያስችላል። ስዊፍት ባንኮችን ተክቶ ለደንበኞች ገንዘብ የሚያስቀምጥ ተቋም አይደለም። ከእዚያ ይልቅ ባንኮች እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ፋይናንሺያል ትራንዛክሽኖችን የተመለከቱ ፋይናንስ ነክ ምስጢራዊ መልእክቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ያቀባብላል። በአጭሩ የአለም አቀፍ ባንኮች አስተማማኝ gmail በመሆን ያገለግላል።

ለምሳሌ ያህል ባንኮች የመተማመኛ ሰነዶች/Letter of Credits ለመከፈት፣ የገንዘብ ዝውውር ትእዛዛትን ገንዘባቸውን ካስቀመጡባቸው ባንኮች ለማዘዝ፣ ኮርፖሬሽኖች የከበሩ ማእድናትና የአክሲዮን ግዢዎችን ለመፈጸም የSWIFT ስርአትን ይጠቀማሉ።

የሩሲያ ባንኮች ከSWIFT ስርአቱ ተቆረጡ ማለት የሩሲያ የአለም አቀፍ ንግድ ላይ ከፍተኛውን ጫና ይፈጥራል። የሩሲያ ባንኮች ወደ ድንጋይ ዘመኑ የቴሌግራም እና የፋክስ ስርአት ለመመለስ ይገደዳሉ። ኢራን ከSWIFT ስርአት የተሰረዘች ጊዜ የወጪ ንግዷ በ2/3 ቀንሷል።

SWIFTን የሚቆጣጠሩት የG-10 ሀገራት ማእከላዊ ባንኮች ሲሆኑ እነዚህም ሀገራት ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣልያ፣ ኔዘርላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ስዊዲን ናቸው። የእነዚህን ሀገራት ማእከላዊ ባንኮች በበላይነት የሚመራው የቤልጅየሙ ማእከላዊ ባንክ ነው።

Tilahun Girma Ango