Get Mystery Box with random crypto!

#ሦስቱ_ዋንኛ_ቀሪ_ትንቢቶች!! (በወንድማችን ተክለኪዳን) ከእንግዲህ ለዓለም ፍጻሜ የሚቀሯችሁ ሦ | የተዋህዶ አርበኞች-Ye Tewahedo Arbegnoch

#ሦስቱ_ዋንኛ_ቀሪ_ትንቢቶች!!
(በወንድማችን ተክለኪዳን)
ከእንግዲህ ለዓለም ፍጻሜ የሚቀሯችሁ ሦስት ዋንኛ ትንቢቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
1. ዓለም ብትመከር፣ ብትገሰጽ፣ እጇን እንድትሰጥ ብትጠየቅ፣ አሻፈረኝ ዲያብሎስ ይበልጥብኛል ብላለች፡፡ እናንተ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ወደ እኔ በንሰሐ አለመለስም ብላችኋል፤ ከእኔ የሆነዉን እዉነት አልቀበልም ብላችኋል፤ እያንዳንዱ አገር የዘራዉን ያጭዳል፤ የዓመፃዉን ፍዳ ይቀበላል፡፡ ይህም የመጨረሻ ፍርዴ ሩቅ አይምሰላችሁ፤ በደጃችሁ ቆሟል፡፡ እኔን ከመፍራትና ከማወቅ ስለራቃችሁ ማስተዋሉን አላገኛችሁም እንጂ ደጃፋችሁን አልፌ ከቤታችሁ ነኝ፡፡

2. ስራና የዓመፃ ልጆችን ከዚህች ምድር ካጸዳዉ በኋላ በእኔ የተመረጠዉ የእናቴ የአደራ እናታችሁ የእመቤታችሁ ምርጥ ባለሟል ለሆነዉ ለኢትዮጵያዊዉ ሰዉ ይህችን የተቀደሰች አገርና ዓለምን በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፡፡ ፈቃዴን ይፈጽማል፤ ያስፈጽማል፡፡ ፈቃዴ ሲፈጸም ይህችን አገርና ዓለምን በምሕረት እጎበኛለሁ፤ መልካም ዘመንን አመጣለሁ፡፡

3. ዘመን መጨረሻ አንድ ቀን አሁን የሚደረገዉን ማጥሪያና ማበጠሪያ ኃይሌን እንዲሁም መልካሙን ዘመን የሚዘነጋ ትዉልድ በዓለም ይወለዳል፡፡ በዚያን ጊዜ ዋናዉ የዓመፃ ልጅ (ሐሰተኛዉ መሲህ) (ሐሰተኛዉ ክርስቶስ) (ሐሰተኛዉ አምላክ) ይነሳል፤ በኃይልና በድንቃድንቅ ተአምራት ለዓለም ይገለጣል፡፡ ለሦስት ዓመት ተኩል (ለአርባ ሁለት ወራት) ብቻ ባለ ጊዜ ሆኖ በእኔ የሚያምኑትን ይፈታተናል፣ ያጠቃል፣ ያሰናክላል፡፡ ትዕቢት የተባሉት የፈርኦን ወንድምና እህቶች፣ ክፋት የተባሉት የይሁዳ ወንድምና እህቶች፣ ዓመፃ የተባሉት የአርዮስ ወንድምና እህቶች የክፉ ትንቢት ፈጻሚዎች በዋናነት ተከታዮቹና አጫፋሪዎቹ ይሆናሉ፡፡ ቁጣዉን በመፍራት አእምሮ ሕፃናትና አእምሮ ቀላሎች ይከተሉታል፡፡ አእምሮ አዋቂዎች ይሰናከሉበታል፡፡ ቁጣዉንና ድንቃድንቅ ተአምራቱን በመመልከት አእምሮ ጽኑአን ይፈተኑበታል፡፡

በሦስት ዓመት ተኩል ዉስጥ በእምነቱ የጸና እርሱ ለሰማያዊ መንግሥት የተመረጠ ነዉ፡፡ የዋናዉ የዓመፃና የዓመፃ ልጆች ባለጊዜነት ስሽር ዓለም እንዳልነበረች ትሆናለች፡፡ የዓመፃ ልጆች በመቅሰፍትና በስቃይ ሞት፣ የተመረጡት ሰዎች ደግሞ በምሕረት ሞት ወደ ማረፊያ ቦታ ይጠራሉ፡፡ በዚህች ምድር ዉስጥ ሆነ በዓለም ዉስጥ በዓይን የሚታዩት፣ የማይታዩት ከመኖር ወደ አለመኖር ያልፋሉ፡፡ የዓለም ፍጻሜ በዚህ መልክ ይጠናቀቃል፡፡” ይላል አልፋና ዖሜጋ እግዚአብሔር፤ የቅዱስ ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል፣ ዑራኤል፣ ፋኑኤል፣ ራጉኤል አምላክ“ ይላል፡፡

ምንጭ "የኢትዮጵያና የዓለም የመጨረሻ ፍርድ አፈጻጸም ዉሳኔ" በመስከረም 2003 ዓ.ም የተጻፈዉና ለሁለተኛ ጊዜ ከታተመዉ ክፍል 2 ምእራፍ 4 ገጽ 55. በተክለ ኪዳን