2022-06-24 17:57:47
ከየትኛው ቀን ላይ ነን?
ሶሎሞን ሰኞ ዕለት ተወለደ፤
ማክሰኞ ከረሰተነ (ክርስቲያን ሆነ)፤
ረቡዕ ጋብቻ መሰረተ፤
ሐሙስ ዕለት ታመመና አመሻሹ ላይ ሆስፒታል ገባ፤
ዓርብ ዕለት ሕመሙ ጠናበትና ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ሞተ፤
ቅዳሜ እረፋዱ ላይ ተቀበረ።
እኛሳ ደግሞ የትኛው ቀን ላይ ነን? ሰው በዚህ ምድር ላይ የሚኖረው ስድስት ቀናትን ያህል ብቻ ነው። ሰባተኛዋ ቀን የዕረፍት ቀን ናት፤ እርሷም የመንግስተሰማያት ምሳሌ ነች። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያሉት ቀናት በዚህ ዓለም ላይ ያለውን ሕይወታችንን የሚወክሉ ሲሆን ሰባተኛዋ ዕለት ዕለተ ሰንበት ደግሞ ከሞት ባሻገር የምንኖረውን ሕይወት ትወክላለች። በስድስቱ ቀናት ውስጥ ዕረፍት እንደሌለ ሁሉ ሰውም በዚህ ምድር ላይ ያለውን እድሜውን አጠናቅቆ እስኪሄድ ድረስ ምንም እረፍት የለውም። ከቀናት ሁሉ ዕለተ ሰንበት እንድትበልጥ ወይም ስድስቱ ቀናት ተጠራቅመው ከዕለተ ሰንበት ጋር ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሁሉ በመንግስተ ሰማያት የምንኖረው የወዲያኛው ዓለም ሕይወታችንም አሁን ከምንኖረው ሕይወት ጋር ሲወዳደር ብልጫውን ስንኳንስ መናገር ማሰብ እንኳን አይቻልም።
ቅዱሳት መፃሕፍት በዚች ምድርና በገነት መካከል ያለውን ልዪነት "ገነትሰ ልዕልት ይእቲ እምዛቲ ምድር መጠነ ምሥራቅ እምዕራብ" /የገነት ልዕልና ከዚህ ምድር ጋር ሲነፃፀር ምሥራቅ ከምዕራብ የሚርቀውን ያህል ነው/ በማለት ሲገልጡ፣ ስለኢየሩሳሌም ሰማያዊትን ግን "ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን ትመስላለች" ከማለት ውጭ ምንም አላሉም። ለሰው ልጅ የመጨረሻውና አንደበት ሊረዳው የማይችለው ታላቁ ደስታ /incomprehensible pleasure/ መንግስተ ሰማያትን ማየት ነው። ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለምና በዚህ ምድር ላይ ምንም surprise የለም።
በዚህ ምድር ላይ በአፀደ ሥጋ ከምንኖረው ከሰባት ቢሊየን በላይ ሰዎች ውስጥ በአሁኗ ሰዓት ከስድስቱ ቀናት ውስጥ በአንዷ የምንገኝ ነን፤
፩ኛ. ሰኞ ላይ ያሉ አሉ እነርሱም በሥጋ ልደት ወደ ዚህ ምድር ከመጡ በኋላ ማክሰኞ ላይ ያልደረሱ ኢጥሙቃን ናቸው።
፪ኛ. ማክሰኞ ላይ ያሉ አሉ፤ እነርሱም እየቀደሱ እያስቀደሱ እየቆረቡም ክርስትናን በተግባር የሚኖሩ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ማክሰኞ ላይ ሆነው ማለት ክርስትናቸው ላይ ፀንተው ቆመው ስለሌሎች ቀናት ረስተው ማለት በዚህ ምድር ላይ ስላላቸውና ስለሚኖራቸው ሕይወት ሳይጨነቁ ከቀናት ሁሉ ለምትበልጠው ለእሁድ ብለው ማለት ለሚበልጠው ለሰማዪ ሕይወታቸው የሚሠሩ ናቸው።
፫ኛ. ረቡዕ ላይ ያሉ አሉ፤ እነዚህ ደግሞ ክርስትናውን ትተው ለትዳር ብቻ ወይም ለመብል ብቻ ወይም ደግሞ ለሌላ ለዚህ ዓለም ትርኪ ምርኪ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ዓለም ቅርጥፍጥፍ አድርጋ የበላቻቸው ሰዎች ናቸው።
፬ኛ. ሐሙስ ላይ ያሉ አሉ፤ እነዚህም የታመሙ ግን ደግሞ ህመማቸውን ችለውና ውጠው የሚውተረተሩ፣ መታመማቸውንም ሰው ያላወቀላቸው ምስኪኖች ናቸው /መታመሙን ሰው ያልተረዳለት ስንት በሽተኛ አለ መሰላችሁ/።
፭ኛ. ዓርብ ላይ ያሉ አሉ፤ እነርሱም በጠና ታመው በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዙና በሞትና በሕይወት መካከል ያሉ ናቸው።
፮ኛ. ቅዳሜ ላይ የምናገኛቸው ደግሞ ሞተው በመቀበር ላይ ያሉ ናቸው።
እኛስ የትኛው ቀን ላይ ነን? ገና እንደተወለድን ምንም መኖር ያልጀመርን ሰኞ ላይ ነን? ወይስ ክርስትናው ውስጥ ማክሰኞ ላይ ነን?
ዓለም የዋጠችን የዕለተ ረቡዕ ሰዎች ነን ወይስ የዕለተ ሐሙስ ታማሚዎች?
አልጋ ላይ ያለን የዓርብ ዕለት ሰዎች ነን ወይስ ተስፋ ቆርጠን ሞተን በመቀበር ላይ ያለን የቅዳሜ ሰዎች?
በድጋሜ የትኛው ቀን ላይ ነን?
155 viewsYeshiwas, 14:57