2021-07-17 23:08:37
╔───────◎◎───────╗
ቢላል ኢብኑ ረባህ
╚───────◎◎───────╝
"አቡበክር ልዑላችን ነው። የኛን ልዑልም ነፃ አውጥቶልናል" የሚለውን የሙገሳ ቃል ሲሰማ ግንባሩን ደፋ፣ ዐይኑን ገርበብ በማድረግ "እኔ ትናንት ባርያ የነበርኩ የሐባሻ ሰው ነኝ" ይላል።
በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሙስሊሞች የኢስላሙን ሙአዚን ቢላል ኢብኑ ረባሕን ያውቁታል። ስሙን፣ ዝናውን እና ሚናውን በሚገባ ያወሱታል።
ሕፃናትን ቢላል ማን ነው ብለህ ብትጠይቅ የረሱል ﷺ "ሙአዚን" ነው ይሉሀል። አሳዳሪው በጋለ ድንጋይ ላይ አስተኝቶ ሲያሰቃየው ወደ ጥንት እምነቱ ከመመለስ ይልቅ "አሐድ... አሐድ... በማለት ፅናቱን የገለፀ ብርቱ ሰው ነበር የሚል ምላሽን ታገኛለህ።
ቢላል ኢስላምን ከመቀበሉ በፊት በሕዝቡ ዘንድ ከእንስሳ ተለይቶ የማይታይ የተናቀ ባርያ ነበር። ኢስላምን ባይቀበል ኖሮ የአሳዳሪውን ግመል ከመጠበቅ ሌላ የህይወት ሚና የሌለው፣ እንኳን ከሞተ በኋላ በሕይወት ዘመኑም አስታዋሽ አልባ ሰው ሆኖ በቀረ።
የመካ ሰዎች በትኩስ ወሬነት የሚነጋገሩት ሙሐመድ ﷺ ነብይ ነኝ ብሎ የመነሳቱ ጉዳይ በቢላል ጆሮ ደረሰ። አሳዳሪውና እንግዶቹ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሲወያዩ ሰማ። በተለይ ኡመያ ኢብኑል ኸልፍ ተንኮል የተሞላበት ውይይትና ምክክር ከጓደኞቹናና ከቁረይሾችች ጋር ሲነጋገር አዳመጠ።
የቢላል ጆሮ ተሰብሳቢዎቹ ከሚናገሩት የጥላቻ ንግግር ውስጥ ረሱል ﷺ ስለተነሱበት አላማና ምን እያሉ እንደሚያስተምሩ ቀነጨበ። አዲስ የመጣው ዲን ለመላው የሰው ዘር ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ሰማ።
በእስልምና በእጅጉ ተማረከ። የኢማን ብርሀን በልቡ ላይ ፈነጠቀ። እምነቱን ይፋ ማድረግ እንዳለበትም ወሰነ። ወደ ረሱል ﷺ በመሄድ ለኢስላም እጁን መስጠቱን ይፋ አደረገ። የቢላል መስለም በመካ ምድር ተሰማ። የበኒ ጀምህ መሪዎች በቁጣ ተወጣጠሩ። በተለይ አሳዳሪው የኢስላም ጠላት ኡመያ ኢብን ኸለፍ ሀበሻዊ ባሪያው መስለሙ እንደታላቅ ነውርና ንቀት ቆጠረው። "ይህ ኮብላይ ባሪያ በመስለሙ ፀሀይ ተመልሳ የምትጠልቅ አይመስለኝም" ሲል ቁጭቱን ገለፀ።
እርቃኑን በትኩስና አሸዋማ መሬት ላይ እንዲተኛ ተደርጎ ቋጥኝ ድንጋይ ደረቱ ላይ ተጫነ። በጠራራ ፀሐይ ሰውነቱ እየተገረፈ "ላት" እና "ዑዛ" የተሰኙ ጣዖታትን እንዲያወሳ ያለ መታከት ይጠይቁታል። መልሱ ግን "አሐድ.... አሐድ" ነበር። "እኛ የምንለውን ደግመህ በል" በማለት ይገርፉታል። በምፀታዊ ቃልም "እናንተ የምትሉትን ለመናገር ምላሴ አትችልም" ይላቸዋል። "ላት" እና "ዑዛ" ጌታዎች ናቸው ካልክ እንተውሀለን በእርግጥ አንተን ማሰቃየት ደክሞናል" ጭንቅላቱን በመነቅነቅ "አሐድ...አሐድ" የሚል ምላሽ ከመስጠት ባሻገር እጅ አልሰጠም ነበር።
አቡበከር ቢላል በሚሰቃይበት ቦታ ደረሱ። "አንድ ሰው አምላኬ አላህ ነው! በማለቱ ብቻ ልትገድሉት ትሻላችሁን?" ሲሉም ጠየቁ። ወደ ኡመያ በመዞር "ቢላልን ከገዛህበት ዋጋ ጨምሬ እከፍልሀለው" ሽጥልኝ አሉት።
ኡመያ በቢላል ተስፋ ስለቆረጠ ገንዘብ ቢያገኝበት የተሻለ መሆኑ ተሰማው። አቡበከር ቢላልን ከገዙት በኋላ ነፃነቱን አወጁ። ቢላልን ተረክበው ሊሄዱ ሲነሱ ኡመያ እንዲህ በማለት ተሳለቀ፦ "በላትና ዑዛ እምላለሁ በአንድ ወቄት ወርቅ ካልሆነ አልገዛህም ብትለኝ እንኳ እሸጥልህ ነበር" አቡበክርም፦ "በጌታዬ አላህ ይሁንብኝ! በመቶ ወቄት ወርቅ ካልሆነ አልሸጥልህም ብትለኝ እንኳ የጠየቅከውን እከፍልህ ነበር" አሉት።
በርካታ የቁረይሽ ሹማምንት በበድር ጦርነት ተሳታፊ ለመሆን በሙሉ ልብ ተነስተዋል። ቢላል ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅም የነበረው ኡመያ ኢብኑል ኸለፍ ግን ከመካ ለመውጣት ባለመፈለጉ ምክንያት ፈጥሮ ለመቅረት አስቧል። ዑቅባ ኢብኑ አቢ ሙዓይጥ ኡመያ ጦርነቱን ላለመሳተፍ ዘዴ እየዘየደ መሆኑን ሲሰማ ሴቶች ጭስ የሚሞቁበትን ሸክላ በመውሰድ ወዳጆቹ በተሰበሰቡበት "የዐሊይ አባት ሆይ! አንተ ሴት ነህና በዚህ ሸክላ ጪስ ሙቅበት" አለው።
ኡመያ የኃፍረት ማቅ መላበሱ ስለተሰማው "አንተንም ሆነ ይዘህ የመጣኸውን ነገር ዑዛ ያጥፋችሁ" በማለት ብስጭቱን ከገለፀ በኋላ ወደ ጦር ሜዳ ለመዝመት ዝግጅቱን ጀመረ።
ውጊያው ተጀመረ። ሙስሊሞች "አላሁ አክበር... አሐድ... አሐድ..." ሲሉ ይሰማል። ኡመያ ይህን ቃል በሚገባ ያስታውሰዋል። ትናንት የቢላል የጣር ድምፅ ነበር። አሁን ደግሞ የአዲሱ ትውልድ መፈክር ሁኗል። ልቡ ተሸበረ። ሠይፍ ከሠይፍ ተፋተገ። አንገት ተቀላ። ከዚህም ከዚያም የጣር ድምፅ ተሰማ። ጦርነቱ ሊገባደድ ተቃረበ። የሙስሊሞች የኃይል ሚዛን ደፍቷል። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ግዙፉን የቁረይሽ ጦር ድል ለመንሳት ተቃርበዋል። ቢላል ኡመያን በግላጭ አገኘው። በተጠማ ሠይፉ "አሐድ... አሐድ... " የሚል መፈክሩን እያሰማ የኡመያን አንገት ቆረጠው።
ቀናት ቀናትን ወልደው አመታት አለፉ። መካ በድል ተከፈተች። ሙስሊሞች መካን አጥለቀለቋት። እውነት... ፈካ... ሐሰት ተነነ። ሰዎች ለድንጋይና ለታቦት መገዛታቸው አከተመ።
ቢላል ከረሱል ጎን ቆሟል። ከካዕባ ጣራ ላይ በመውጣት የ"አዛን" ጥሪን እንዲያሰማ አዘዙት። በታላቁ ቦታ በተከበረው ቀን ሐበሻው ቢላል በካዕባ አናት ላይ በመውጣት "አዛን" አሰማ። በሺህ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች እርሱን በመከተል የአላህን መልእክት ደጋግመው አስተጋቡ።
ቢላል ከረሱል ﷺ ጎን ሳይነጠል ኑሮውን መግፋቱን ቀጠለ። እርሳቸው በተገኙበት ዘመቻ ሁሉ ዘምቷል። ሁሌም ለሶላት "አዛን" ያደርጋል። ከጨለማ ወደ ብርሀን፣ ከባርነት ወደ ነፃነት ያወጣውን ታላቅ ዲን አርማ ያስተጋባል።
አንድ ለራሱና ለወንድሙ ሚስት ለማጨት ወደ ሴቶቹ አባት ቤት አመራ። "እኔ ቢላል እባላለሁ ይህ ደግሞ ወንድሜ ነው። ሀበሻዊ ባሪያዎች ነን...በተሳሳተ እምነት ላይም ነበርን። አላህ መራን። ነፃ አወጣን። ልጆቻችሁን ከዳራችሁልን አልሀምዱሊላህ እንላለን። ከከለከላችሁን ደግሞ አሁ አክበር እንላለን" በመተናነስ ጠየቀ። ጥያቄው ተቀባይነት አጊኝቶ ሀላ ቢንት አውፍን አገባ።
ከረሱል ﷺ ህልፈት በኋላ አዛን ማድረጉን አቁሞ በጂሃድ መስክ ላይ ተሰማራ። ዑመር ኢብኑል ኸጣብ ለጉብኝት ሻም በገቡበት ወቅት የሻም ነዋሪዎች ለአንድ ጊዜም እንኳ ቢሆን ቢላል አዛን ያሰማቸው ዘንድ ዑመር ግፊት እንዲያደርጉ ጠየቁ። ቢላል በልመና ተስማማ። አዛን አሰማ። "አሽሃዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉላህ" የሚለውን ሐረግ ጮኾ ለማሰማት ሳግ ያዘው። ዕንባ ተናነቀው። የረሱል ﷺ ትዝታ በአዕምሮው ተቀርፆ ትንፋሽ አሳጠረው። እርሱና በረሱል ﷺ ዘመን የነበሩ ሰሐቦች በእንባ ተራጩ። በተለይ ዑመር እንባቸውን ለረጅም ጊዜ መግታት አልቻሉም።
አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸው
╔───────◎───────╗
ምንጭ:
كتاب: رجال حول الرسول
╚───────◎───────╝
ለሌሎችም ሼር በማድረግ ተደራሽነቱን እናስፋ በእናንተ ሰበብ አንድ ሰው ወደ መልካም ነገር ቢመራ እኩል አጅርን ይጎናፀፋሉ
@yemrtoche_twlede
112 views˙·٠•● Abuki ●•٠·˙, 20:08