2022-07-10 00:05:36
"ምጥን የእሁድ ምስባክ"
ርዕስ፦ “የሕይወትን/የአገልግሎትን ሩጫ እንዴት እንሩጥ?” (ክፍል-3)
የንባብ ክፍል=ዕብ12፡1-2
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮሩ የመጽሐፉ ቁልፍ ጥብጦች መካከል፦
ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ እና ፍጹም ሰው ነው (1፡1-4፣ 2፡5-18)፣
ይህ መጽሐፍ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነትና ሰውነት በተገቢው ሁኔታ ዘግቧል። የኢየሱስን ፍጹም ሰውነት ስንቃኝ፦
1) እንደሰው ጸልዮአል# ስለጸሎትም አስተምሯል፤ እንደሰው ተፈትኗል በፈተናውም አልፎ የሚፈተኑትን ይረዳል፤ እንደሰው መከራ ተቀብሏል በመከራ የምንጸናበትን/የምንታገስበትን አቅም ይሰጠናል፤ እንደሰው ሞቷል ከሞት ፍርሃት ነፃ አውጥቶናል!
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የመጨረሻው የእግዚአብሔር መገለጥ፣ ፈጣሪ፣ የፍጥረት ደጋፊ/መጋቢ (1፡1-14)
ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም እንከን የሌለበት ሊቀ ካህን ነው (1፡3፣ 2፡10-18፣ 4፡15-16፣ 9፡10-11፣ 19)፣
ሊቀ ክህነቱም ከመልከጸዴቅ ጋር ተነጻጽሯል፣ ራሱ ካህን ነው እዲሁም እንከን የሌለበት መስዋዕት ነው፣ ካህኑ በነገር ሁሉ የተፈተነ ስለሆነ የሚፈተኑትን የሚረዳና የሚረዳ ነው፣ ምንም ኃጢአትን አላደረገም፣ ክህነቱም በሞት ምክንያት የሚገታ ሳይሆን በሰማይም የሚቀጥል ነው፣ እርሱ ለራሱ መስዋዕት መቅረብ አላስፈለገው ለሌሎች ቤዛነት እንጂ፣…
ኢየሱስ ክርስቶስ ከነቢያት፣ ከመላዕክት፣ ከአሮጌው ኪዳን፣ ከአሮን ክህነት፣ ከመገናኛው ድንኳን/መቅደስ፣ ከብሉይ ኪዳን መስዋዕት፣… ይበልጣል (1፡4-2፡18፣ 3፡1-6፣ 5፡1-10፣ 7፡1-10፣18)፣
የሁሉም ነገር ፍጻሜ በኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያ ምጽዓቱ ተጀምሯል በዳግም ምጽዓቱ ይጠናቀቃል (1፡2፣ 9፡9-28፣ 12፡22-29)።
ክርስቶስ ላይ ማተኮር ስንል፡-
ክርስቶስን መመልከት/በእርሱ ላይ ማተኮር ቅጽበታዊ እይታ ሳይሆን ሁልጊዜ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሕይወታችን መልዕቅ፣ ሮል ሞዴል፣ የድልና የአሸናፊነታች መሰረት ማድረግ ማለት ነው፣
ውጤታማ የእምነት ሩጫ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ዓይንን/ አትኩሮትን በማሳረፍ የሚመጣ ነው፣
እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በክርስትና ሩጫ ውስጥ የሚገጥመውን ፈታኝ ሁኔታዎች ክርስቶስ ላይ በማተኮር በጽናት ሊወጣቸው ይገባል፣
የክርስትናን ሩጫ ክርስቶስን በመመልከት የሚሮጥ ሩጫ ነው፤ ለዚህም ክርስቲያኖች ክርስቶስን እንዲመለከቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል (12፡1-2፤ 6፡11-12፤ 3፡1-2)፣
በዘመናችን ያለችውም ቤተ ክርስቲያንም በዘመኑ ካሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ራሷን ለማስመለጥ እንድትችል ዛሬም አይኗን በክርስቶስ ላይ አድረጋ መሮጧ አማራጭ የሌለው አስገዳጅ ነገር ነው፣
ኢየሱስ እንከን የሌለበት የእምነት ሯጭ መሆኑን በእረኝነቱ፣ በመሪነቱ፣ በካህንነቱ፣ በአስተማሪነቱ፣ በአገልጋይነቱ፣ በጽናቱ፣ በትዕግሥቱ፣ በማይቀፍ ሕይወቱ፣ ወዘተ አሳቷል።
ኢየሱስ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ነው
“ራስ” (originator, founder, leader, pioneer) “የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት…” (ሐዋ. 3፡15)፣ “…ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።” (ሐዋ. 5፡31)። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ እንደመሪ ሌሎችን የሚያስቀድም ትሁት መሪ ነው (ዮሐ. 13)።
“በፊቱ ስላው ደስታ መስቀሉን ታግሦ የመስቀሉን ውርደት ንቆ” (ዓመት)
“በፊቱ ስላለው ደስታ”፡ የኢየሱስ ሩጫ ግብ ያለው ሩጫ ነበር። ይህም ነፍሱን ለኃጢአተኞች ቤዝዎት በመስጠት የሚያጠናቅቀው ዋንኛ ደስታው ነበር። የኢየሱስ ደስታ በእርሱ የመስዋዕትነት የመስቀል ሞት የሚድነውን ከቁጥር በላይ የሆነ ሕዝብ ወደ ፊት አሻቅቦ ተመልክቶ የመስቀሉን ውርደት ታግሷል (ማር. 10፡45፣ ዮሐ. 15፡11፣ ሉቃ. 10፡20-21)።
“የመስቀል ሞት”
ኢየሱስ የእምነትን ሩጫ ከግርግም እስከ መስቀል በሚገባ ሮጦ የፈጸመ ሯጭ ነበር (ሉቃ.2፡7፤ ዮሐ.17፡3-4፣ 19፡30፤ ፊል.2፡8)
ክስ (ወንጀለኛነት/ እርግማን፣ ግርፋት፣ መዘባበቻ መሆን፣ ምራቅ መተፋት፣ ጥፊ፣ ስድብ፣ ፌዝ፣ በጦር መወጋት፣ አጥንት መሰበር፣ የእሾህ አክሊል፣ መቸንከር፣ መስቀል ተሸክሞ ረዥም ጉዞ ማድረግ፣ ጥም (የባሕርና የውቅያኖስ ፈጣሪ)፣ በአምላክ መተው፣… (ፊል. 2፡6-8)፣“በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው። (ዘዳ. 21፡23፣ ገላ. 3፡13)፣
መስቀል የጣር ስፍራ፣ የመተው ስፍራ፣(ማቴ.27፡46)
በመስቀል ላይ ጌታ ኢየሱስን የተገረፈው፣ የተቸነከረውን ቁስል በዝንቦች እንኳን ሲበላ እሽ ማለት አለመቻል (ኢሣ. 53፡4-6)፣
ጌታ ኢየሱስ ስቃዩን ለማደንዘዝ/ለመርሳት በባህላዊ ማደንዘዣ አልወሰደም (ማቴ.27፡34)!
በመስቀል ላይ ሸክሙን ለመያዝ ወደላይ መሳብና የተቸነከረበት ሚስማር የሚፈጥረው መተልተል፣… ማሰብ ከአእምሮ በላይ ነው!
በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና
“እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (2)
ጌታ ኢየሱስ ሰው በመሆን በቤተልሔም የጀመረው ሩጫ እስከ መስቀል ሞት በመሞት እስከታችኛው ወለል ድረስ ዝቅ በማለት ትህትናን አሳይቷል። መክበሩ ደግሞ ከሞት በመነሳት፣ በማረግና በአባቱ ዙፋን ቀኝ በመቀመጥ አሳይቷል።
ጌታ የመጨረሻ የሚባለውን በመስቀል የመሞት ጽነትና ትዕግሥትን ምሳሌ፦
“…በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤…” (ፊል. 2፡1-12)
ማጠቃለያ፦ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው የክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት በሩጫ የተመሰለ የሕይወት ዘይቤ ነው። ሩጫው እጅግ ትዕግሥትንና ጽናትን የሚጠይቅ እደሆነ እሙን ነው። ሩጫውን የጀመረ ሁሉ ደግሞ አይጨርስም። ስለሆነም በዚህ የሕይወትና የአገልግሎት ሩጫችን በውጤታማነት ለመጨረስ በእምነት የሩጫ ሜዳ ላይ በመፋለም ሩጫቸውን የጨረሱትን የእምነት አባቶች ጽናት ዋቤ በማድረግ (11 እና 1ሀ)፣ ለውጤታማ ሩጫ እንቅፋት የሚሆኑ ሸክሞችንና የኃጢአት ልምምዶች ከሕይወታችን በማስወገድ (1ለ) እንዲሁም የሃይማኖታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህን (3፡1)፣ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ (12፡1-2) በሆነው በክርስቶስ ላይ በማተኮር ሩጫችንን በጽነት ልንፈጽም ይገባናል።
እግዚአብሔር የጸጋ ሁሉ አምላክ ይርዳን!
አበቃሁ!!
ዘሪሁን ታከለ (አስተማሪ )
@yemengedusewoch
@SolenTse
+251941214813
329 viewsSolomon Tsegaye, 21:05