Get Mystery Box with random crypto!

በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ | የማርያም መቀነት

በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ ነፃነቷን አስመልሳለች፡፡ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ_ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት ሰቀሉ፡፡ ጣሊያን ከአድዋ ሽንፈት 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደራጅቶ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረ፡፡


ከአድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር ለ8 ወራት በፅናት ተዋጋች፡፡የጊዜዎቹ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም፡፡የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በአውሮኘላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ አብይ አብይ ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ ፣ እቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ፡፡


ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር /ሊግ ኦፍ ኔሽንስ/ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ የሚሰማቸው ግን አላገኙም፡፡አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀናጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው፡፡ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩ፡፡የ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች፡፡ ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ፡፡

ስለዚህም ወታደራዊ ድገፍ ሰጥተው ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው፡፡በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ ፤ በጄሪራል ኘላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ ፤ ከዚያም ከሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ጌዲዮን ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ፡፡በመካከለኛ ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃትቸውን አፋፋሙ፡፡ ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ፡፡ በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ተነገረ፤ ዘመቻው ከተጀመረ 2 ወራት ሳይሞላው ፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡መጋቢት 28/1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡

እንግሊዞች ኢትዮጵያውን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው፡፡ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ፡፡

ንጉሰ ነገስቱም ሚያዚያ 27 በአዲስ አበባ ታላቁ ቤተ-መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ፡፡በአርበኞች ታላቅ ተጋድሎ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት በልጆቿ መስዋዕትነትና የደም ማኅተም ነፃነቷን አፀናች፡

ክብር ኢትዮጵያን በክብር ላቆዩን አባት አርበኞቻችን!