Get Mystery Box with random crypto!

✞ እንኩዋን ለታላቁ ሊቅ 'ቅዱስ ያሬድ' ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ታላቁ | የማርያም መቀነት



✞ እንኩዋን ለታላቁ ሊቅ "ቅዱስ ያሬድ" ዓመታዊ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ :- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን : ክብራችን : ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን?

አንደበቱ ጣፋጭ [ጥዑም] : ልቡናው የቅድስና ማሕደር : ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው:: እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ!

ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት :- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ: ሙሉ አካሏ ነው"

የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ :-

ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ፭፻፭ [505] ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና [ታኡክልያ] አባቱ ደግሞ ይስሐቅ [አብድዩ] ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር [ትምሕርት] አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ::

ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ:: ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው::

ትሏ ፮ [6] ጊዜ ወድቃ በ፯ [7] ኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና:: ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ: ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ::

ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው:: ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ:: በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር::

ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: ፫ [3] መላእክት በወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት: ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር: ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::

ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ: ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ::

ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት :-

፩. ፭ "5" ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል::

፪. በጣና ቂርቆስ: በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል::

፫. በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል::

በ፭፻፸፮ [576] ዓ/ም በተወለደ በ፸፩ [71] ዓመቱ ተሰውሯል::

አባቶቻችን :-

- ጥዑመ ልሳን
- ንሕብ
- ሊቀ ሊቃውንት
- የሱራፌል አምሳያ
- የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
- ካህነ ስብሐት
- መዘምር ዘበድርሳን
- ማኅሌታይ
- ልዑለ ስብከት
እያሉ ይጠሩታል::

የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን::

" እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ::" [፪ቆሮ.፲፪፥፪-፭] (12:2-5)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]