Get Mystery Box with random crypto!

ያን ጊዜ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመብረቅ ላይ ተጭኖ በረረ እነዚያ አጋንንት ወደአሉበትም ወ | የማንቂያው ደውል 🔔🔔🔔

ያን ጊዜ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመብረቅ ላይ ተጭኖ በረረ እነዚያ አጋንንት ወደአሉበትም ወረደ። ደመናትም ከበቡአቸው መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሩአቸው በመብረቅም አጨዱ አቸው አመድም ሆነው በነፋስ በተኑአቸው። የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባት መቶ ሺህ እልፍ ከአንዱ ሺህ ነበር። ከዚህም በኃላ ጌታ ክርስቶስን የካዱ ወዳሉበት ወደ ምእራብ ሀገር ወሰደው። ነገስታቱና መሳፍንቱ መኳንንቱም በሚወጡበትና በሚገቡበት ጉዳና ላይ አቆመው ጌታችንም በዚች ጉዳና ብዙ መከራ ያገኝሀል ግን በርታ ታገስ ብሎት በዚያ ተወው። በዚያን ጊዜም የአርብ ንጉስ ጣዖታቱን አስይዞ መኳንንቱን ሰራዊቱን አስከትሎ በዚያች ጎዳና መጣ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን በጎዳና ውስጥ በተገናኙት ጊዜ ጣኦታቱ ወድቀው ተሰባበሩ።

ንጉሱም አባታችንን በአየው ጊዜ አንተ ጠጉር ለባሽ ምንድነህ ሰው ነህን አለው።አባታችንም አዎን ክብር ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያው የሆንኩ ሰው ነኝ ብሎ ለከሀዲው ንጉስ መለሰለት። ንጉሱም ዳግመኛ አባታችንን በዚያ አይሁድ በሰቀሉት ታምናለህን አለው አባታችንም በሰው ፊት አምንበታለሁ።ስለ እኔ በተሰቀለው አላፍርበትም ስለ እኔ ብቻ የተሰቀለ አይደለም ስለ አንተና ከአንተ ጋራ ስለ አሉትም ነው እንጂ ንጉስ ሆይ የዘላለም ህይወትን ታገኛላችሁ እመኑበት አለው።

ንጉሱም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ተቆጣ ሰራዊቱንም ጠርቶ በፍጥረት እሳትን አንድዱ ለተሰቀለው ለናዝሬቱ ሰው ባሪያው ነኝ የሚለውን ጠጉር ለባሽ ወስዳችሁ ጨምሩት አላቸው።የእሳቱም ነበልባል በረጅም ዛፍ መጠን ከፍ ከፍ እስከሚል አነደዱ። አባታችን ግን ንጉሱና ሰራዊቱ ሁሉ እያዩት አልፎ በፈቃዱ ወደ እሳቱ ገባ። እሳቱም እንደወንዝ ውኃ ሆነ ሰረዊቱም እጅግ አደነቁ እኩሌቶቹም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ንጉሱም ሲያደንቁ በአየ ጊዜ ፈፅሞ ተቆጣ ከሰባ ሰባት አርበኞቹ ጋራ በቁጣ ተነስቶ ያደነቁትንና ያመኑትን አንገታቸውን ቆረጠ ።

በዚያችም ቀን የተቆረጡ አርባ መቶ ሺህ ሆነው ተቆጠሩ።ንጉሱም የአባታችንን አንገት ሊቆርጥ ሰይፉን መዞ ተወርውሮ ሄደ። ያን ጊዜም ከመብረቅና ከነጎድጓድ ጋራ ታላቅ ንውፅውፅታ ሆነ ንጉሱንም ከሰራዊቱ ጋራ አጠፋው ከከሀዲው ንጉስ ጋራ የሞቱት ቁጥራቸው አራት ሺህ እልፍ ሆነ።

ጌታችንም አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጠላቶችህንና የኔንም ጠላቶች አጠፋሁልህ አለው።አባተችን ግን በመብረቅ የሞቱትን ሬሳቸውን ነፍሳቸውንም መላእክተ ፅልመት ወደ ስቃይ ሲወስዱአቸው በአየ ጊዜ መድኃኒታችንን እሊህን ስሁታን ማርልኝ ሰው ስሁትና ከዳተኛ ነውና አቤቱ አንተ ግን መሀሪ ይቅር ባይ ታጋሽም ነህ አለው።አባታችንም ይህን ሲናገር ጌታችን ተሰወረ።

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም ከዚያ ሄደ ታላቅ ገደልም አገኘ እግሮቹንም በገመድ አስሮ በገደሉ ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ።ሰይጣንም መጥቶ ያቺን ገመድ ቆረጣት ወደ ታችም ተወርውሮ ወረደ።ቅዱስ ሚካኤልም ቀድሞ አባታችንን ያዘው በእግርህ ላቁምህ ወይም በራስህ አለው በራሴ እቆም ዘንድ ተወኝ አለው ትቶት ሄደ።

በዚያም በራሱ ቁሞ በጥርሶቹም ደንጊያ ነክሶ እስከ ሰላሳ አመት ኖረ አንጀቱና ናላው ሁሉ እየፈሰሰ አልቆ መላ አካሉ እንደእንጨት ቅርፊት ሆነ። ከሰላሳ አመትም በኃላ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችንን ገብረ መንፈስ ቅዱስ እያለ ሶስት ጊዜ ጠራው። እርሱም እነሆኝ ጌታዬ አለ ጌታችንም እነዚያን ከሀዱዎች ምሬልሀለሁ ከዚህ ተነሳ አለው።ያን ጊዜ የነከሰውን ደንጊያ ትቶ ተነሳ።ጥርሱም ተነቅሎ በድንጊያ ተተክሎ ቀረ። ክንፎችም ተሰጥተውት እየበረረ ከእግዚአብሔር ፊት ደረሰ ጌታውንም ከማርክልኝ ከስጋቸው ጋራ ተነስተው በመጠመቅ ክርስቲያኖች ይሁኑ ብሎ ለመነው። መድኃኒታችንም በሽተኞችን ልትፈውስ ሙታንን ልታስነሳ ስልጣን ሰጥቼሀለሁ አሁንም ወደተገደሉት ሄደህ በመስቀል ምልክት በላያቸው አማትብ ህይወት መድኃኒት በሆነ ስሜም አስነሳቸው አለው።ያን ጊዜም በድኖቻቸው ወዳሉበት ሂዶ አስነሳቸው አጥምቆም ክርስቲያኖች አደረጋቸው ከእርሳቸውም ሄደ።

ከዚህ ዓለም የሚለይበት በቀረበ ጊዜ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ ተገለጠለት። ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ እስከ አስራ አምስት ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን ሰጠው።የእድሜውም ዘመናት አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ሲሆን በሰላም በፍቅር አረፈ። ጌታችንም ነፍሱን ተቀበለ አቅፎም ሳማት በመላእክትና በቅዱሳን ሁሉ ምስጋና አሳረጋት።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)