Get Mystery Box with random crypto!

‹‹ባል አስይዞ ቁማር›› ምዕራፍ-13 ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ከአስር ጊዜ በላይ ደውሎላት ነበር | የልብ ቃል ሚዲያ

‹‹ባል አስይዞ ቁማር››
ምዕራፍ-13
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ
ከአስር ጊዜ በላይ ደውሎላት ነበር ቀልቧ ቃል ላይ ተለጥፎ ስለነበረ አላነሳችለትም ..እና አሁን ለዛ ነው እየደወለችለት ያለችው፡፡
አነሳላት‹‹‹ምነው አንቺ ይሄን ሁሉ ስደውል?››
‹‹አላየሁትም ነበር..ስልኬን መኝታ ቤት ጥዬ ሳሎን ነበርኩ….››
‹‹ምን አስዋሸሽ ማሚ ጋር ደውዬ መኝታ ቤትሽ እንደሆንሽ ነግራኛለች፡፡››
‹‹አይ አንተ ሰው..ስለእኔ ዘበኞችንም ቤት ሰራተኞችንም እናቴንም መጠየቅ አይደክምህም?››
‹‹እንደዛ እንዳላደርግ ከፈለግሽ ስፈልግሽ ተገኚያ››
‹‹እሺ……››
‹‹በቃ ለንቦጭሽን አትጣይ..ንፍቅ ብለሺኝ እኮ ነው፡፡››
‹‹እንዴ ጥዋት እኮ አብረን ነበርን››አለችው…ስልክ ስላላነሳችለት ብቻ እንዲህ መንጨርጨሩ አስገርሞታል…ምን ሳታደርግና ምን ሳታስብ የእሱን ስልክ እንዳላነሳች እውነቱን ቢያውቅማ ጨርቁን እንደሚጥል እርግጠኛ ነች፡፡
‹‹እኔ እኮ እንደአንቺ ደንዳና ልብ የለኝም…ለሰከንድም ባትለይኝ ደስ ይለኛል… በጣም እኮ ነው የማፈቅርሽ››
‹‹እኔም አፈቅርሀለሁ››ለምን እንደሆን ባታውቅም ይሄን ቃል ምን አልባት ከሺ ጊዜ በላይ ለእሱ ተጠቅማለች፡፡ከልቧ ደስ ብሏትና የእውነቷን ነበር ቃሉን ከአንደበቷ የምታወጣው….፡፡ዛሬ ግን ከበዳት ….እየሻከረት ነው የተናገረችው፡፡
‹‹…ፍቅርን እያቆሸሽኩት ይሆን እንዴ?…..ቺት እያደረኩብት ይሆን እንዴ…?ምን ያደረኩት ነገር አለ….? ተጀናጀንኩ.. ተሳሳምኩ..ምን ፈፀምኩ….?›› ብላ እራሷን ለማፅናናት ብትሞክርም ልቧ ግን ለሆነ ሌላ ሰው መቅለጥ መጀመሯን መዋሸት አልቻለችም…፡፡
ከእዚህ ጉድ ለመውጣት ቶሎ ይሄን ሰው ማግባት እንዳለባት ቅፅበታዊ ውሳኔ ወሰነች ‹‹…ልዩ ሳትወራጂ ይሄን ነገር አድርጊው››እራሷን መከረች…እና ወዲያውኑ ወደተግባር ተሸጋገረች፡፡
‹‹ስማ…›
‹‹ወዬ የእኔ ፍቅር…››
‹‹ደግሞ ሸጉጠሀኝ ውለህ ሸጉጠኸኝ ማደር ከፈለክ ጠቅልሎ ማግባት ነዋ…››
‹‹ምን?››
‹‹አዎ ሰምተሀል…››
‹‹መለመን ከጀመሪኩ እኮ አመት ሊያልፈኝ ነው…አንቺ ነሽ ሰበብ እየፈጠርሽ ስታዘገይው የነበረ፡፡››
‹‹ለትምህርቴ ብዬ ነዋ..አሁን ደግሞ ለምርቃት ሶስት ወር ነው የቀረኝ፡፡››
‹‹አንቺ የሆነ ሀሳብ መጣልኝ..፡፡››
‹‹ምንድነው ?ልስማው…››
‹‹ለምን አንድ ቀን አናረገውም…?ማለቴ አንድ ቀን እንኳን ባይሆን ተከታታይ ቀን ይሁን..፡፡ ››
‹‹አይ አንደዛ አይሆንም.. ሁለቱንም ለየብቻ ነው ማጣጣም የምፈልገው… ግን ምርቃቴንና ቀለበቴን በአንድ ቀን ማድረግ እንችላለን፡፡
‹‹አሪፍ ነው…ግን ቀለበት አስሮ ብቻ አንድ ቤት መግባት ይቻላል እንዴ?››
‹‹አዝናለሁ እንደዛ አይቻልም፡፡››
‹‹ወይ ታዲያ ምንድነው ትርፌ?››
‹‹በወሩ ደግሞ ሰርግ ይሆናላ…››
‹‹ምሽቱን ሙሉ ስታበሳጪኝ ያመሸሽው እንዲህ አይነት የሚያስፈነጥዝ ዜና ልታሰሚኝ ነው…..በስመአብ ….በጣም ነው የማፈቅርሽ..››
‹‹እኔም አፈቅርሀለሁ..በል ደህና እደር..፡፡››
‹‹ደህና እደሪ …ደግሞ ነገ አላልኩም እንዳትይ….ንግግራችንን ቀድቼዋለሁ››
‹‹የሰው ድምፅ ያለፍቃድ መቅዳት ወንጀል እኮ ነው፡፡››
‹‹የሰው ድምፅ አልቀዳሁም ፤የሚስቴን ነው…የሚስቴ ድምፅ ማለት ደግሞ የራሴ ነው፡፡››
‹‹በል ይሁንልህ… ቸው፡፡›
‹‹ቸው››
ስልኩን ዘጋችና በድንጋጤ ጭንቅላቷን ያዘች‹‹…ልዩ ምድነው የሰራሽው…? አሁን ከአራት ወር በኃላ ሚስትና የቤት አስተዳዳሪ ለመሆን ዝግጁ ነሽ……?ልጅ ወልደሽስ ማሳደግ ትችያለሽ…?.›› እራሷን አምርራ ብትወቅስም አንዴ ከአንደበቷ ያወጣችውን ቃላት ሰብስባ መልሳ ልትወጣቸው አልችለችም፡፡
‹‹….እስኪ ገና ለገና ፍቅር ከሌላ ሰው እንዳይዘኝ ተብሎ ያልሆነ መክለፍለፍ ውስጥ ይገባል…?››እራሷን አምርራ ወቀሰች፡፡
ከልጁ ፍቅር እንዳይዛት ቀላል ዘዴዎች ነበሩላት..ለምሳሌ እቤቱ አለመሄድ… መኝታ ቤቱ የቀበረችውን መከታተያ እንዳይሰራ ማበላሸት…ስልኩን ከስልኳ ላይ ማጥፋት…በቃ ካልደወለችለት እንደማይደውልላት እርግጠኛ ነች..እቤቱ ካልሄደች እሱ እቤቷ አይመጣም…ጭራሽ አድራሻውንም አያውቀውም…ታዲያ ከእሱ ፍቅር እንዳይዛት ልትወስድ ያሰበችው እርምጃ ምን የሚሉት ነው .. በቅፅበታዊ ውሳኔዋ እራሷን ጠላች …
ግን ፍቅር እንዳይዘኝ እንዳይዘኝ የምትለው እስከአሁን አልያዘትም ማለት ነው…..?ፍቅር ያዘት ተብሎ በእርግጠኝነት የሚወራው የፍቅሩ መጠን ምን ያህል ሲሆን ነው? መለኪያውስ ምንድነው?ይህንን እሷስ ታውቀዋለች?
እና ደግሞ አሁን በዚህ ሰአት ቃል ከተኛበት ተነስቶ ከራሷ ኮሚፒተር እሱ ቤት በደበቀችውን ካሜራ ሀክ አድርጎ እሱን መኝታ ቤቱ የሚያደርገውን እያየች እያሳየች የነበረውን ስሜት መድሀኔ ጋር ደውላ ስለመጋባት የተነጋገረችውን ስልኩን ከዘጋች በኋላ በተናገረችው ተፀፅታ ስትቆጭ ጠቅላላ ቆይታዋን ሰምቶ ተገርሞ መልሶ እንደተኛ ብታውቅ ምን ትል ይሆን?

ይቀጥላል...
https://m.youtube.com/@-yelebkalmedia1237