Get Mystery Box with random crypto!

መነጠል እና መጀመል ... ይልቅ አንድ ታሪክ ልንገርህ፡፡ እ.ኤ.አ በ1750ዎቹ በለንደን ከተማ | የሀሳብ መንገድ

መነጠል እና መጀመል

... ይልቅ አንድ ታሪክ ልንገርህ፡፡

እ.ኤ.አ በ1750ዎቹ በለንደን ከተማ ጎዳናዎች የሆነ የሚያስገርም ሰው ብቅ አለ፡፡ ስሙ ጆናስ ሀንወይ (712-1786 እ.ኤ.አ) ይባላል፡፡ የሆነ ቀን ከጨርቅና ከቆዳ ቀጣጥሎ የሠራውን ዘባተሎ ግዙፍ ጃንጣለውን ይዞ ብቅ ሲል "ምን ጉድ ነው? "በሚል ስሜት ሰዎች ተከተሉት፡፡ ጃንጥላውን ይዞ በወጣ ቁጥር አንድ ገበያ ሕዝብ ያጅበው ጀመር፡፡ ምናልባት የሚሸነቁጥ የሚያዋርድ ስድብም ይከተለው ይሆናል፡፡ ለሠላሳ ዓመታት ይሄው ምቾት የሚነሳ አጅብ አልቀረለትም፡፡

እነሆ ዛሬ በአሜሪካ ብቻ በዓመት 33 ሚሊዮን ጃንጥላዎች ይሸጣሉ፡፡ 365 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ለግብይቱ ይውላል፡፡ ከኛም ሀገር የመከላከያ በጀት እንደሚወዳደር ልብ በልልኝ፡፡ በዘመናዊው ዓለም በዓለማቀፍ ደረጃ እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ጃንጥላ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ዛሬ ጃንጥላዎች ከዝናብና ሀሩር መከላከያነታቸው በተጨማሪ የውበት፣ የፋሽን መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ሌላም ነገረ ሀቲታችን የሚያሰፋ ተረክ እነሆ..

በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን አንድ ቀን የሙዚቃው ጠቢብ ቪትሆቨንና ወልፍጋንግ ገተ በእግር እየተንሸራሸሩ ሳለ ድንገት አንድ መስፍን በመንገዳቸው ላይ እስከ አጃቢዎቹ መጣ፡፡ ገተ መንገድ ለቆ ሲሽቆጠቆጥ ቪትሆቨን ግን ከመንገዱ ንቅንቅ አላለም፡፡ መስፍኑ ለምን መንገድ እንደማይለቅ ቪትሆቨንን በጠየቀወም ጊዜ አለ

«ልዑል ሆይ አንተ ልዑልነትን የተቀዳጀኸው በመወለድ ብቻ ነው፡፡ አዕላፍት ልዑላን ነበሩ፡፡ ሌሎች ሺዎች ልዑላን ወደ ፊት ይኖራሉ፡፡ ነገርግን አንድ ቪትሆቨን ብቻ...›› ቪትሆቨን ቪትሆቨንን ለመሆን ግን አርባ ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ የመስማት ችሎታውን አጥቷል፡፡ ይህ በሞዛርት አንደበት ሳይቀር አድናቆት የዘነበለት የረቂቅ ሙዚቃ (classical music) ጠቢብ ቪትሆቨን
በዕድሜ ዘመኑ አጋማሽ ቀስ በቀስ መስማት አቆመ፡፡ ነገሩ እጅግ አስደንጋጭ ሆነበት፡፡ ራሱን እስኪጠላ ድረስ ተረበሸ፡፡ በዝናብ ውስጥ ለረጃጅም ሰዓታት ጠዓረ ሞት መስሎ ተመላለሰ፡፡ ተቅበጠበጠ፡፡ ራሱን ለማጥፋት ዳዳው፡፡

በመጨረሻ አዲሱን ማንነቱን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ከዓለም ተገለለ፡፡ ተነጠለ፤ የሌለ ያህል ተረሳ፡፡ ራሱን ሙዚቃዊ ፈጠራዎቹ ውስጥ ቀብሮ እሱ የማይሰማውን የረቂቅ ሙዚቃ ጥዑም ውህድ ማረቀቁን ተያያዘው፡፡ አስደናቂዎቹን ፈጠራዎቹን የሠራው መስማት ካቆመ በኋላ ከዚህ ሕመም፣ ከዚህ የመነጠል፣ የመገለል ጥልቅ ውስጥ ነበር፡፡ የተጋፈጠው ፈተና ግን የምንጊዜም ምርጥ የረቂቅ ሙዚቃ (classical music) ሰዎች ተርታ ከመመደብ አላገደውም፡፡ ከገጠመው መራር ዕጣ ጋር ተናንቆ እንዴት የሕይወት መንገዱን እንደቀየረ ሲናገር ‹‹ዕጣ ፋንታዬን ጉሮሮው ላይ ፈጠረቅሁት፡፡ ብሏል፡፡ ዛሬ ትውልድ በየዕለቱ በሥራዎቹ እየተደነቀ የዓለምን መልክ ከቀየሩ መቶ ሰዎች መሃል ደምሮ ያስታውሰዋል፡፡

ስሙን ለማስታወስ የተቸገርኩት አንድ ሰው ሳነበው የገረመኝ አንድ ሀሳብ አለው፡፡ በአንድ ዐረፍተ ነገር ብቻ ሲቀርብ «human mind is a gigantic duplicating machine)) ይሆናል፡፡ ዘመኑን በሚሊዮንም ስፈረው በሺኅ የሰው ልጅ ከአደን ዘመን ጀምሮ ያሳየው የኑረት ዘይቤ መሻሻል በጣም ጥቂት ነው፡፡ ብዙው ሰው ኢምንት ሳያበረክት በስህተት እንደተጠራ ተጀምሎ ሲቆጠር ኖሮ ያልፋል፡፡

ሱሪያሊቱ ሠዓሊ ሳልቫዶር ዳሊ የሴትን ልጅ ውበት ከአበባ ጋር ያመሳሰለው የመጀመሪያው ሰው እሱ ፈላስፋ ነው፡፡ የደገመው ግን ደደብ ነው፡፡» ይላል፡፡ አልበርት ካሙም በካሊጉላ አንደበት ‹‹አያትህን መብለጥ ካልቻልክ አስቀድሞውኑ ሞተህ መቀበር ነበረብህ፡፡›የሚል ግልምጫ ሰንዝሯል፡፡ ብዙ ሰው በኑረት ለዛው እንደ ተፈጥሮ ስህተት የሚቆጠር ምንም ነው፡፡ የአያቱን ዳዊት የሚደግም የአባቱን ሙታንታ የሚታጠቅ ስርዝ ድልዝ ነገር፡፡ ይኼን ጽሑፍ የማንበብ ተነሳሽነቱ ያለህ አንተ ይኼን እንደ ስህተት መቆጠርን የምትጸየፍ ይመስለኛል፡፡

አሜሪካዊቷ አብስትራክት ሠዓሊ አንግሥ ማርቲን ።በሕይወትህ ውስጥ እጅግ መልካም የሚባሉት ነገሮች የሚከሰቱልህ ብቻህን ስትሆን ነው፡፡›› ትላለች፡፡ አየህ ዛሬ እኛ የምንኖርበትን ንቅሳታም አለም የገነቡት ነጠል ብለው መቆም የቻሉ፣ ሌላ ዓይነት የህይወት ቅኝት የነበራቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ያለውን ዘመናዊ ስልጡን ዓለም አንድ በአንድ የቀረጹት ሕይወትን በተለየ እንግዳ ዓይን የታዘቡት፣ ከተራ ምልከታ ተነስተው ነባሩን ዘልማዳዊ ዓለም የሚቀይር ሀሳብ ያረቀቁት ነበሩ ።

ምንጭ-ከባዶ ላይ መዝገን
ደራሲ- ያዕቆብ ብርሀኑ

@yehasab_menged
@yehasab_menged