Get Mystery Box with random crypto!

​​#ዝክረ_መነኮሳት #ተሳሕያን_መነኮሳት ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ °°°°°°°°°°°°°°°° | የአባቶቼን ርስት አልሰጥም

​​#ዝክረ_መነኮሳት
#ተሳሕያን_መነኮሳት

ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°

በዚህች ቀን ሕይወቱ እጅግ ታላቅ የሆነ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት አረፈ። ይህ ቅዱስ መንግስተ ሰማያትን በኃይል ነው የወሰደው። ልክ ጌታችን በወንጌል እንዳለ:-

"...መንግስተ ሰማይ ትገፋለች ግፈኞችም ይናጠቋታል(በኃይል ይወስዷታል")__ማቴ 11:12

ቅዱስ ሙሴ በቀደመው ሕይወቱ ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች ባሪያ ነበር። አብዝቶ መብላት እና መጠጣት የሚወድ ኃያል ሰው ነበር። በመግደል፣ በመዝረፍ እና በክፋት ስራ ሁሉ ውስጥ ነበር፤ ማንም ሰው በፊቱ ሊቆምም ሆነ ሊቃወመው አይችልም ነበር። ብዙ ጊዜም አይኑን ወደ ፀሐይ አንስቶ "ኦ ፀሐይ አንተ አምላክ ከሆንክ አሳውቀኝ" ይል ነበር። ከዚያም በኋላ "የማላውቅህ ሆይ ራስህን ግለጥልኝ" ይል ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን የሆነ ሰው በገዳም ያሉ አባቶች እውነተኛውን አምላክ ያውቃሉ፣ ወደነርሱም ሂድ ይነግሩኃል ሲል ሰማ። ፈጥኖም ተነሳ ሰይፉን ታጠቀ ወደ አስቄጥስ በረሃ ተጓዘ። አባ ኤስድሮስንም አገኛቸው፣ ባዩትም ጊዜ ስለ አመጣጡ ፈርተው ነበር። ቅዱስ ሙሴ ግን መነኮሳቱ ስለ እውነተኛው አምላክ ለማወቅ እንዲያስተምሩት እንደመጣ ነገሮ አረጋጋቸው። ቅዱስ ኤስድሮስ ወደ አባ መቃሪዮስ ታላቁ ወሰደው፤ እርሱም ሃይማኖት አስተምሮ አጠመቀው። ካመነኮሰው በኃላ በገዳም መኖርን አስተማረው።

ቅዱስ ሙሴ በብዙ አምልኮ መትጋት ጀመረ፣ ከብዙዎቹ ቅዱሳን የበለጠ ጽኑ ተጋድሎን ተጋደለ። ነገር ግን ዲያብሎስ በቀደሙት ልማዶቹ አብዝቶ በመብላት፥ በመጠጥ እና ዝሙት ክፉኛ ተዋጋው። ሁሉንም በተጋድሎው የመጣበትን ነገር ለቅዱስ ኤስድሮስ ይነግረው ነበር። እርሱም ያበረታታዋል፥ የጠላትን ደባ እንዴት እንደሚያሸንፍ ይነግረዋል።

የገዳሙ አረጋውያን በተኙ ጊዜ እንስራቸውን ወስዶ ከገዳሙ ረዥም ርቀት ተጉዞ ውሃ ይቀዳላቸው ነበር። ከብዙ አመታት መንፈሳዊ ትግል በኃላ ሰይጣን ቀንቶበት እግሩን አሳመመው በዚህም የተነሳ አልጋ ቁራኛ አደረገው። ይህም ከሰይጣን መሆኑን ሲያውቅ አምልኮቱን እና ትሕርምቱን ጨመረ፥ በዚህም ሰውነቱ እንደ ተቃጠለ እንጨት ሆነ።

እግዚአብሔር ትዕግስቱን ተመልክቶ ሕመሙን እና መከራውን አራቀለት። የኢየሱስ ክርስቶስ በረከትም በርሱ ላይ ሆነ። ከተወሰነ ጊዜ በኃላ የ500 ወንድሞች አባት እና መንፈሳዊ መሪ ሆነ። እነርሱም ካህን እንዲሆን መርጠውት ነበር። ክህነት ሊቀበል ወደ ፓትርያርኩ ሲመጣ ትዕግስቱን ለመፈተን አረጋውያኑን " ይህን ጥቁር ማነው እዚህ ያመጣው? ከዚህ አውጡት" አሏቸው። ሙሴም ታዞ ወጣ ለራሱም እንዲህ አለ "አንተ ጥቁር ያደረጉልህ ነገር መልካም ነው(የውስጤን ጥቁረት ቢያዩስ ኖሮ እያለ በትህትና)"። ፓትርያርኩም መልሰው ጠርተውት ካህን አድርገው ሾሙት፥ እንዲህም አሉት "ሙሴ አሁን ውስጥህም ውጭህም ነጭ ሆነ"።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርዮስ ታላቁ ሄደ። እርሱም "ከእናንተ መሃል የሰማዕትነት አክሊል የሚቀበል እንዳለ አያለሁ" አላቸው። ቅዱስ ሙሴም መልሶ "ምናልባት እኔ እሆንን? 'ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ' ማቴ 26:52 ተብሎ ተጽፏልና። ወደ ገዳሙ ከተመለሱ በኃላ ብዙም ሳይቆይ በርበሮች ገዳሙን አጠቁት። ወንድሞችን "መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ" አላቸው። ወንድሞችም "አንተስ አባታችን ለምን አትሸሽም?" አሉት። እርሱም ይህን ጊዜ(ሰማዕትነቱን) ለረዥም ጊዜያት ሲጠብቀው እንደነበረ ነገራቸው።

በርበሮች ወደ ገዳሙ ገብተው ከሌሎች ሰባት ወንድሞች ጋር ገደሉት። ከወንድሞች አንዱ ተደብቆ ነበር፥ የጌታ መልአክ አክሊል ይዞ እየጠበቀው መሆኑን ሲመለከት ከተደበቀበት ወጥቶ ሰማዕትነትን ተቀበለ።

ተወዳጆች ሆይ በንስሐ ሀይል ላይ ተመሰጡ እንዲሁም ምን እንዳደረገ ተመልከቱ። አንድ አረማዊ፥ ነፍሰ ገዳይ፥ ዘማዊ እና ዘራፊ ባሪያ የነበረን ሰው ወደ ታላቅ አባት፣ መምህር፣ አጽናኝ እና ለመነኮሳት ስርዓትን የጻፈ ካህን እንደለወጠው። ስሙም ዘውትር በጸሎታት ሁሉ ይጠራል። ቅዱስ አጽሙ አሁን በወንድማማቾች ማክሲሞስ እና ዶማዲዮስ ገዳም(ኤል-ባራሙስ) ይገኛል።

ጸሎቱ ከኛ ጋር ትሁን፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፤ለዘላለሙ አሜን