2022-05-28 07:22:52
ሪፍቅ (ልስላሴ)
አላህ ለፍጡራኖቹ አዛኝ ነው። ለዚህም ስለሆነ በተውሂድ ያዛቸዋል፣ ሽርክን
እንዲርቁ ያስጠነቅቃቸዋል። በተውሂድ ላይ ኖረው፣ ሽርክን ከነባለቤቶቹ
ርቀው፣ በተውሂድ ላይ ከሞቱ ጀነት የሚባል ልብ ጠርጥሮት፣ ጆሮ ሰምቶት፣
አይን አይቶት የማያውቅ አገር ተዘጋጅቶላቸዋል።
በተገላቢጦሹ አዛኙ አላህ፣ ፍትሃዊ፣ አያያዙ የበረታ፣ አሸናፊ ፈራጅ ነውና በሱ
ላይ የሚያጋሩትን "አጋርያን እርኩሶች (ነጃሳዎች)" ናቸው ሁሉ ብሎ
ጠርቷቸዋል። በዱንያ ውርደትን፣ በአኸይራ አሳማሚ ቅጣትን
አዘጋጅቶላቸዋል። አላህ ይጠብቀን።
ልክ እንደዚሁ ለአማኞች ከነፍሳቸው በላይ የሆኑት ውዱ የአላህ መልክተኛ
(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) አዛኝ ናቸው። በጣም አዛኝ ከመሆናቸውም የተነሳ
ሰዎችን ዘላለም አለም እሳት ውስጥ የሚከታቸውን ሽርክ
1) እያዩ እንዳላዩ ዝም አላሉም፣
2) በሽርክና ቢድአ ጉዳይ ላይ አንድ ነን ብለው አልተስማሙም፣
3) ወደ ሽርክና ቢድአ የሚጣራን አይደለም ወደነዚህ መንገድ የሚወስዱን
ነገሮች ዝም አላሉም።
በጣም አዛኙ ነብይ ስለ ቢድአ ሲያስጠነቅቁ ፊታቸው ደም ይለብስ ነበር፣
ይቆጡ ነበር ምክንያቱም ቢድአ ነውና የዚህ ኡማ ትልቁ ፀር።
ስለ ሪፍቅ ሲወራ ባይጠቀስም አብሮት ሺዳ በውስጡ አለ።
እዝነትም (ልስላሲ)፣ ጥንካሪም ቦታ ቦታ አላቸው። መቼም አንድ ዳኢ ሽርክን
ስለሚያክል ታላቅ አደጋ እያስተማረ ለምን ይኮሳተራል? ተብሎ ሊጠየቅ
አይገባውም። ምክንያቱም የነብያትም፣ በተለይ የነብዩ ሰለላሁ አለይሂ
ወሰለምም አካሄድ ይሄ ነበረና።
ቢድአና ወንጀልንም ለያይተን ማስቀመጥ አለብን። የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ
አለይሂ ወሰለም ዘንድ ወንጀለኞች (መጠጥ ጠጪዎች፣ ዝሙት የሰሩ) ሲመጡ
የነበረውን አቀባበል አንርሳ። ልስላሲ ነበር ከመልክተኛው ሰለላሁ አለይሂ
ወሰለም የነበረው። እኚሁ የአላህ መልክተኛ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጁምአ
ኹጥባቸው ላይ "አዳዲስ በዲን ላይ ያሉ ፈጠራ ጭማሪዎችን ተጠንቀቁ፣
ሁሉም ፈጠራ ጥመት ነው፣ ሁሉም ጥመት የእሳት ነው" ሲሉ ምን ያህል
ይቆጡ እንደነበር የሀዲስ መዛግብትን ማየት ይበጃል።
አንድ እናት ልጇን ብትገርፍ፣ አንድ አባት ልጁን ቢቆጣ እንዲስተካከልላቸው
እንጂ ጠልተውት አይደለም። ስለሱ የማይጨነቁ ቢሆን ኖሮ ልጃቸውን
ከነመጥፎ ባህሪው ይተውት ነበር።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ መጥፎ ነገር ሽርክ፣ ቢድአ፣ መሀይምነት፣ ድራማ፣ ፊልምና
የመሳሰሉት ተስፋፍተው ሲያዩ የአላህ ባርያዎች ስለሚያዝኑ ነው ለኡማው ያ
ሁሉ ውርጅብኝ ከየአቅጣጫው እየወረደባቸው ሀቁን የሚናገሩት። አላህም
ለባሮቹ ስለሚያዝን ነው አዛኝ ከመሆኑም ጋር ማስጠንቀቂያዎችንና ዛቻዎችን
አብሮ ያስቀመጠው። ነብዩ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለምም እንደዚሁ እዝነት
በሚያስፈልገው ቦታ እዝነት፣ ጠንከር ማለት በሚያስፈልገው ቦታ ጠንከር
ብለው ያሳዩን።
አሁን ያለንበት ወቅት ላይ በጣም እዝነት ያስፈልገዋል ይህ የማይካድ እውነታ
ነው። ይህ ማለት ግን ቢድአና ሙብተዲ ላይ አለመናገር ማለት አይደለም።
ቢድአና ሙብተዲ ላይ መናገር ለኡማው በጣም እጅግ በጣም ከማዘን ነው።
ምክንያቱም ኢስላምንና ሙስሊሞችን ከውስጥ የሚንደውና የሚያዳክመው
አዳዲስ መንገዶችና የቢድአ ሰዎች ናቸውና።
አላህ ሁሉንም በቦታው ላይ ከሚያስቀምጡት ባርያዎች ያድርገን። አላህ ሆይ!
እውቀትን ጨምርልን፣ በምናውቀውም የምንሰራ አድርገን፣ በፈተና ወቅትም
በሃቅ ላይ ከሚፀኑት አድርገን።
@wumjbot
418 views04:22