2022-04-05 18:27:32
ማስያስ ናይን
.
.
.
በቅናት ተሞልተው -ለክሳቸዉ ፅሕፈት-ነዉርን ቢያጡብህ፤
አይሁድ ተመካክረው-ምስክርን ገዙ-አደፍ ቢታጣብህ።
አይቶ ላስተዋለ-ልቆ የሚሰማ-ከአይሁድ ጫጫታ፤
ከንግግር በልጦ-ልብ የሚጠረጥር-ረጅም ዝምታ።
እንደምን ያለ ነው?
ምራቅ እየተፋ-ዲያቢሎስ አዳምን-ሲኦል እንዳስገባዉ፤
ጌታችን ተዋርዶ-ምራቅ ተተፍቶበት-ዳግመኛ ሊክሰዉ፤
ልምዳቸው እንዳይቀር-በርባንን ፍታልን ብለው ሲጠይቁ፤
ክርስቶስን ሰቅለው-ወንጀለኛን ገደልን-ብለው ሊራቀቁ።
የሾህ አክሊል -ጎነጎኑ -ከራሱ ሊያኖሩ፤
ሶኩን አቀዳጅተዉ-ንግሥናውን ሽረዉ-ሞቱን ሊናገሩ፤
ስቀለው!እያሉ - ሩህሩሁን ጌታ-ፍትሕን ነፈጉት፤
ንዋይ በገዛቸዉ-በሀሰት መሳክርት-ሞትን ፈረዱበት።
ስቀለው! ስቀለው !ይሰቀል !
የሚሉ ጩኸቶች -ከዛ ካደባባይ-አይለዉ ሲሰሙ፤
በጥላቻ መንፈስ -ፊቱን ተመልክተው-ሌሎች ሲራገሙ፤
መዝሙረኛው ዳዊት-በትንቢት መነፅር-ቀድሞ ተመልክቶ፤
በዉሻ አይሁዶች-የቀራኒዮዉ በግ-መከበቡን አይቶ።
"ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን
ወአኀዙኒ ማህበሮሙ ለእኩያን
ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን "
እንደምን ያለ ነው ?
ህመምን ፈዉሶ-ጎባጣ ያቀናን አልባስክን መገፈፍ፤
ከእጅህ በጎረሰ-ካንተ በተማረ -ወንበዴ መገረፍ።
ዉሃን የፈጠረ-ዉሃ ተከልክሎ-ሀሞት ሲቀርብለት፤
በሰፈነግ ሞልተው-ሆምጣጤ ቅልቅል-ቀድተው ሊያጠጡት፤
መራራ መጠጡን -ቀመሰና ተወዉ-ሊጠጣ አልወደደም፤
ለወጉት ከሳሾች-ሰድበው ለተፉበት-በቀል አልተመኘም።
ድንግሊቱ ታለቅሳለች-ከመስቀሉ ስር ተደፍታ፤
በመስቀል ዉሎ እያየች-ልጇ ሲንገላታ፤
ከደረቱ የተጠጋው -ታማኙ አገልጋይ-ትህትናን ያዘለዉ፤
እናቱ ትሆን ዘንድ-እሱ እንዲሆን ልጇ-አደራ ተሰጠዉ።
የአለም ብርሃን-ተከሶ ብታየዉ-ጠሀይቱ ጨለመች፤
የፍጥረታት ጌታ-መሞቱን ብታየው-ጨረቃ ደም ሆነች።
ዮሴፍ ወ ኒቆዲሞስ -በሐር በፍታ ገነዙት፤
መግነዙን አስረው-ባዲስ መቃብር አኖሩት።
ጌታችን ተነሳ- በሃይሉ-መቃብሩን ፈነቃቅሎ፤
በሥልጣኑ- ነፃ አወጣን -ሞታችንን ገድሎ፤
በፍቅር ተስቦ-ነፍሳትን አወጣ-ሲኦልን መዝብሮ፤
እብለት የሌለውን -ትንቢቱን ፈፀመ-ዲያቢሎስ አስሮ።
ግን እኔስ????
ከትንቢቱ ፍፃሜ-ከሞትና ትንሣኤው -አብሬ ያልተባበርኩ፤
ከመርከቢቱ ተኝቼ-ከጥልቁ ባህር የሰመጥኩ፤
መንገዱ የጠፋብኝ-በሃጢአት ሸክም የጎሰቆልኩ፤
ከቤት ርቄ-ስቅበዘበዝ-ማረፊያ አጥቼ፤
ወደ ኩነኔ የገባሁ-የፅድቅ መንገዱን ትቼ፤
ኪሪያላይሶን -ማረኝ አትለፈኝ፤
እንደቸርነትህ-ከእቅፍህ አስገባኝ።
የክፋትን መርዝ-በማር ለዉሼ-የምሸጥ፤
ከመቅደስህ ሰርቄ-ለመቅደስህ ስመፀዉት፤
ያቺን መክሊት -ቀበርኳት-እንዳተርፍበት ከሰጠኸኝ፤
ቆፍሬ አኖርኳት-ሸጬ ለዉጬ-ሳልገኝ፤
እብኖዲ ናይን -አምላክ ሆይ!ማረኝ፤
መፃጉዕ ነኝና- አይተህ አትለፈኝ።
ወንጌልን ሰምቼ-በሌላኛው ጆሮ-ዘፈን ስሰማበት፤
ቆሞ ባስቀደሰ-በክቡር አካሌ-እየጨፈርኩበት፤
ዘወትር ከደጅህ -የምገኝ-መንፈሴ ካንተ የራቀ፤
ብኩን ከንቱ -መሆኔ-አለማወቄን ያሳበቀ፤
ማስያን ናይን- መሲሕ ሆይ! ማረኝ
ለምፅ የወረሰኝ-ድዉይ ነኝና -አምላኬ ማረኝ፤
ማስያስ ናይን-መሲሕ ሆይ! ማረኝ።
639 views£di_wub , 15:27