2022-08-18 21:30:29
የዚህ ቤት ባለቤት ፥ ጥሩነሽ ዲባባ
(በእውቀቱ ስዩም)
የጠዋት እቅልፍን ከነፍሴ በላይ እወዳለሁ፤ጫጫታ እጠየፋለሁ፤ አንዳንዴ መላ ከተማውን “ ሳይለንት ሞድ “ ላይ ማድረግ ቢቻል እንዴት አሪፍ ነበር ብየ እመኛለሁ፤ የጥንት የጎጃም ደብተራዎች የነጋሪት ድምጽ የሚዘጋ ድግምት ነበራቸው ይባላል፤ በሚቀጥለው አገር ቤት ስሄድ የዚህን ምስጢር ማጣራት አለብኝ ፤
ዛሬ ጠዋት ፥ ከበድ ያለ የትርምስና የጫጫታ ደምጽ ቀሰቀሰኝ፤
ካልጋየ ላይ እየተቅመደመድሁ ተነስቼ ፤ እየተራገምኩ በሩን ከፈትኩት:
:
አምስት ጩጨዎች ናቸው፤ ከቁመታቸው እሚበላልጥ ዱላ ይዘዋል፤ እያንዳንዱ ዱላ ጫፉ ሁለት ሶስት ቆርኪ ስለተንጠለጠለለት፥ በረንዳየን በወቀረው ቁጥር ባንዴ የከበሮና የጽናጽል ድምጽ ያወጣል ፤ ዋናው አስጨፋሪ ልጅ ከሌሎች ልጆች በውፍረትም በቁመትም የሚብልጥ መዛጊያ የሚያክል ዱላ ይዟል፡: የዱላ አያያዛቸው ፥ከጭፈራው ጎን ለጎን ህብረተሰቡን የማስቦካት አላማ እንዳላቸው ያሳብቃል፤
“ መጠናል ባመቱ
አረ እንደምን ሰነበቱ”
ሲል ጀመረ ባለመዛጊያው፥
አቡሽ! የዛሬ አመት እዚህ አገር አልነበርኩም፤ ጭፈራውን ለምን በቀደዳ ትጀምረዋለህ? ነውር አይደለም እንዴ?
ጩጨዎቹ ግሳጼየን ከመ-ጤፍ ሳይቆጥሩ ሆታውን ተያያዙት ፤ ፤ አንደኛው ልጅ አይናፋር ብጤ ነው ፤ ሆታውን አይቀበልም፤ ዝምታውን ለማካካስ በረንዳየን በዱላው በሀይል ይወቅጠዋል፤
“እዚያ ማዶ !
ሆ !
አንድ አበባ !
ሆ !
እዚህ ማዶ አንድ አበባ!
ሆ
የዚህ ቤት ጌታ
ሆ!
ጥሩነሽ ዲባባ”
አለ አስጨፋሪው፤
“ እኔ የቤቱ ተከራይ ነኝ ፤ ቢሆንም፤ ሙገሳውን ለባለቤቱ አስተላልፋለሁ” አልኩ፤
አስጨፋሪው በቃሉ የያዘው ጭፈራ ሲያልቅበት ፤ ከኪሱ ቢልቦርድ እሚያክል ወረቀት አወጣ፤
“ በቃ! በቃ! እንኩዋን አደረሳችሁ፤ ዛሬ ኪሴ ውስጥ ገንዘብ ስለሌለ በሚቀጥለው አመት ተመለሱ “ ብየ ልገባ ስል፤ አስጨፋሪው ፤
“ በሞባይል ባንክ ትራንስፈር ልታረግልን ትችላለህ” አለኝ
ትውልዱን እየተራገምኩ፥ ወደ ቤት ገባሁና ተመልሼ ወጣሁ፤ አስጨፋሪው የሰጠሁትን አስር ብር አገላብጦ በቅሬታ አይቶ ወደ ኪሱ ከጨመረ በሁዋላ ተከታዮቹን እየነዳ መውረድ ሲጀምር “ እግረመንገዳችሁን ይቺን ይዛችሁልኝ ውረዱ “ አልሁና በረንዳየ ጥግ ላይ በግብዳ ብጫ ፌስታል ቁዋጥሬ ያስቀመጥኩትን ቆሻሻ ብድግ አድርጌ አቀበልኩዋቸው ፤
ሁለተኛውን ደረጃ ከወረዱ በሁዋላ አስጨፋሪው ቀና ብሎ እያየኝ እንዲህ ሲል ሰማሁት “
“ የወፍ ፋፋ የወፍ ፋፋ
አንተ ሶየ ተነፋ “
ወደ ምኝታቤት ተመልሼ አልጋየ ላይ ስወጣ ፤ ሁለተኛው ዙር የጩጨ ባንድ በረንዳየን መውቀጥ ጀምሯል፤
@WAS143
@WAS143
1.5K viewsWasye, 18:30