Get Mystery Box with random crypto!

#የመዘምራን_አለቃና_እረኛ #መጋቢ_ደበበ_ለማ ዘሪሁን ግርማ እኛ ስንጠራ | የዘር ሐሳቦች/ Yezer Hasaboch

#የመዘምራን_አለቃና_እረኛ #መጋቢ_ደበበ_ለማ
ዘሪሁን ግርማ

እኛ ስንጠራው "ጋሽ ደቤ" (በታላቅ አክብሮትና ፍቅር ጋር) እንለዋለን። በጣም የተወደደ የቤተክርስቲያን አባት፥ የመዘምራን አባት የተወደደ እና በመዘምራን (Choirs) አንጻር እጅግ በብዙ ሺዎች ዘማሪያን ያፈራ እና ቀዳሚ ፈር ቀዳጅ ከምንላቸው ነው ጋሽ ደቤ። በቅርቡ ዘማሪ ሳሚ ተስፋሚካኤል 'ስላገለገልከን እናመሰግናለን' ብሎ ባዘጋጀው የመዝሙር ኮንሰርት ላይ ካባ አልብሶ አመሰግኖታል። ጋሽ ደቤ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመዘመራን አለቃ ሆነህ በብዙ ዘማሪያን ስላፈራህ፥ ስላገለገልከን እኛም እናመሰግናለን። የጋሽ ደቤ አገልግሎት ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ስለ ስራው ስራ ሁሉ ለማውራት አይደለም። እሱን በተመለከተ "የተፈጸመ ጥሪ" በመጋቢ ደበበ ለማ ቦጋለ የህይወት ታሪኩንና፥ የአገልግሎት መንገዶቹን ጽፎልናል። ገዝተን እናንብብ። እኔ ጥቂት ስለ ጋሽ ደቤ የማውቀውን

መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ " መጋቢ ደበበ ለማ በአዲስ አበባ በቀድሞው የጽዮን መዘምራን፥ በመሪነትና በሙዚቃ ተጨዋችነት ያገለገለ ወንድም ነው። ብዙዎቹን ዝማሬዎች በቃሌ አጥንቻለሁ።
በአገልግሎቱ ስር ያደጉ ብዙዎች፥ መጋቢ ደበበን እንደ አባት ያዩታል..." ያላሉ።

ሐዋሪያው ዳንኤል ጌታቸው ደግሞ "...ከደበበ ጋር ከልጅነት ጀምሮ የምንተዋወቅ ሲሆን፣ በኃላም በእግዚአብሔር ቤት አብረን አድገናል። በተለይም የላይኛይቱ ጽዮን በመባል በምትታወቀው ጸሎት ቤት፣ ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ጌታን ስናገለግል በዚያ ወቅት ነበር ለእኔና ለፓስተር ደበበ የአገልግሎት ጥሪ የደረሰን። 1961-1964 በነበረን አስደናቂ ጊዜ የጌታን ክብር ዐብረን ተለማምደናል።" ይላሉ።

ጋሽ ደቤ ጌታን የተቀበለው በ1959 ሲሆን በጌታ ጥሪን ተቀብሎ ማገልገል የጀመረው በ 1967 ነበር። ጌታን እንደተቀበለ ጌታን እሱን ለአገልግሎት የሚፈልገው በመዘምራን አገልግሎት አቅጣጫ እንደሆነ ነገሮታል "አንተ የመዘምራን አለቃና እረኛ ነህ.." እንዳለው ጋሽ ደቤ አጫውቶኛል።

ጋሽ ደቤ ለአገልግሎት የጌታን ጥሪ ከተቀበለበት ጀምሮ የአገልግሎቱን አቅጣጫ በዝማሬ፤ በሙዚቃ እና ኳየሮችን በማደራጀት ላይ አተኩሮ ላለፉት አርባ አምስት አመታት በላይ አገልግሏል። በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ የጋሽ ደቤን ያህል መዘምራንን ያደራጀና፥ ብዙ ዝማሬዎችና መዘምራንን ያፈራ ሰው በታሪክ አላውቅም። በግሌ አለ ብዬ አላምንም።

#የመዘምራን_ህብረቶች (Choirs) ጋሽ ደቤ በሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን የተቋቋሙ የC መዘምራን 115 ፣ D' መዘምራን 240 ፣ E' መዘምራን 240፣ ኢዮሳፍጥ መዘምራን 280 ፣ የኮተቤ ሙሉ ወንጌል መዘምራን 30 መዘምራንን ያቀፉ ኳየሮችን መስርቶ አደራጅቷል። ጋሽ ደቤ በየ ክፍለ ሃገር እየሄደ የተለያዩ ኳየሮችን እያሰለጠነ የመዘምራንን ህብረት (Choirs) አደራጅቷል። ጋምቤላ፥ ሆሳዕና፥ ደሴ፥ መቀሌ፥ ደምቢዶሎ፥ ነቀምቴ፥ ሃዋሳ፥ ኦሞ ሸለቆ፥ ሾኔ አርባምንጭ፥ ባኮ፥ ፊንጫ ይገኙበታል። ጋሽ ደቤ "የተፈጸመ ጥሪ" የተሰኘውን የህይወት ታሪኩን እንዲሁም በዝማሬ ዙሪያ "አምልኮ መዝሙርና መዘምራን" የሚል መጽሐፍ ጽፏል። ይህ መጽሐፍ ወደ ኦሮምኛ ጭምር ተተርጉሞ ይገኛል። ጋሽ ደቤ አኮሪዲዮን እየተጫወተ ያገለግላል።


#የሶሎ_ዘማሪያን ጋሽ ደቤ አሁን በሶሎ ዘማሪነት የምናውቃቸው ዘማሪንንም አፍርቷል ከእነዚህ መሐል "...ዘማሪ ሳሙኤል ተስፋሚካኤል፥ ዘማሪ ዮሴፍ ካሳ፥ ዘማሪ ወድማየሁ የልቤ፥ ዘማሪ ኤፍሬም ዳኜ፥ ዘማሪ ዮሐንስ በላይ፥ ዘማሪ ሔኖክ አዲስ፥ ዘማሪ ሳሙኤል ንጉሴ፥ ዘማሪ አማኑኤል በፍቃዱ እና እጅግ እና ወደ 20 የሚጠጉ ሶሎ ዘማሪያን በዚህ አገልግሎት እንዲወጡ ጋሽ ደቤ ብዙዎቹን አስተምሯል።

መጋቢ ደበበ ለማ (ጋሽ ደቤ) ለ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን፥ አጠቃላይ በአገራችን ላለው የዝማሬ አገልግሎት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ብዙ ፍሬዎችንም አፍርቷል። መላው የኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናትን ጠቅሟል። ጋሽ ደቤ ስላገለገልከን እናመሰግናለን። እንወድሃለን።