Get Mystery Box with random crypto!

#የዘመኑ 'የታገቢኛለሽ' #ጥያቄና_አኪያሄዱ!! ዘሪሁን ግርማ 'የታገቢ | የዘር ሐሳቦች/ Yezer Hasaboch

#የዘመኑ "የታገቢኛለሽ" #ጥያቄና_አኪያሄዱ!!
ዘሪሁን ግርማ

"የታገቢኛለሽ ወይ" ጥያቄ የሚቀርብበት የእንግዳ- ክስተት?! (Surprise) ቀን ላይ የመገኘት፤ በአንዳንዶቹ ላይ ፕሮግራም የመምራት አጋጣሚዎች ነበሩኝ። የእጮኝነት የቀለበት ፕሮግራሞች መደረጋቸው ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም። አኪያሄዱና የአላማው ምንነት ላይ ግን ሁሌም ጥያቄ አለኝ። ለእህቶች ክብር የሚደረግ ነገር ተንበርክኮ "የታገቢኛለሽ" ጥያቄ መጠየቁም ላይም ምንም ተቃውሞ የለኝም። ለእህቶቻችን በዚህ መልኩ ክብር መስጠቱ መልካም ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ መሆን የሌለባቸው ሶስት ነገሮችን ላንሳ አብሶ እንደ ክርስቲያን!!

፨ #ግነት አንዳንድ የእጮኝነት ቀለበት ፕሮግራም ግነት ይበዛዋል። ከአለባበስ ጀምሮ እስከ አጠቃላይ ፕሮግራሙ የተጋነነና የእወቁልኝ ፕሮግራም ይመስላል። አንድ ሰው የአንድን ሰው ሰርግ አየና "ባለፈው ተጋብተው አልነበር እንዴ?" ብሎ ጠየቀኝ ለካስ የእጮነት ቀለበት ፕሮግራሙ በጣም የተጋነነ እና ሰርግ በሚመስል ደረጃ የጮኽ ነበር። ከእጮኝነት ቀለበት በላይ ሰርጉ አለ፤ ከሰርጉ በላይ አብሮ መኖሩና ኑሮን መጀመሩ የበለጠ ዋጋን ይጠይቃልና አትኩሮትን ትዳር ላይ ማድረግ ወሳኝ ነው። ሰው ሲሰለጥን አይደለም የታገቢኛለሽ ወይ ጥያቄን ሰርጉን በመጠኑ ነው የሚያደርገው።

፨ #በዚህ ጊዜ ያሉ የታገቢኛለሽ ጥያቄዎች ብዙዎቹ እንግዳ-ክስተት (Surprise) አይደለም! ይህ የማወራው ሁሉንም የሚወክል ባይሆንም አብዛኛዎቹን ይመለከታል ብል ግነት አይመስለኝም። እንግዳ-ክስተት ነው ካልን ልጅቷ በምንም በማታውቅበት መንገድ፤ ባልታሰበበት መንገድ ወንድየው ብቻ ተዘጋጅቶ የሚያቀርበው "የታገቢኛለሽ ወይ" ጥያቄ መሆን አለበት። ፈረንጆቹ ይህን አይነት ጥያቄ ሲያቀርቡ ሴቷ በምንም አታውቅም ያ ነው እንግዳ-ክስተት (Surprise) የሚሆነው። አሁን የጀመርነው አኪያሄድ እንግዳ-ክስተት አይደለም ሴት ወይ ታውቃለች ወይም ትጠራጠራለች። ከዚህ ሁሉ ግርግር ባላሰበችበት ጊዜ ምንም ሳትዘጋጅ የታገቢኛለሽ ወይ? ጥያቄን ማቅረቡ ወጪም ይቀንሳል ውበትም ይኖረዋል።

፨ #ሽማግሌ ከተላከና ቤተሰቦችዋ ጋብቻውን ከተቀበሉ በኃላ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ማቅረቡ አኪያሔዱ ትክክል ነው ብዬም አላምንም። ሁለቱ ባህሎች የማይገናኙና የማይጣጣሙ ናቸው። ሽማግሌ ከተላከ በኃላ እንደምታገባው ያውቃል የታገቢኛለሽ ጥያቄ ማቅረቡ ለምን ያስፈልጋል? እሷን ቀድሞ ደግሞ ታገቢኛለሽ ወይ ብሎ ጠይቆ እሷ "አዎ" ካለችው በኃላ ሸማግሌ ሲላክ ቤተሰቦችዋ ባይቀበሉስ ምን ያደርጋሉ? እነዚህን ነገሮች እንዴት እናስታርቃቸው? መልሱን ለእናንተ!

በመጨረሻም፦ ሁሉም በአግባብና በስርአት ይሁን። እንደ ክርስቲያን ደግሞ ኑሮው ላይ እንጂ ግርግሩ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ነው። ግንነት የሌለበት፥ በእውነትም እንግዳ ክስተት (Surprise) (ምንም በማይታወቅና ልጅቷ ባላሰበችበትና በማትጠራጠርበት ጊዜ፥ ቦታና ሁኔታ ውስጥ ቢደረግ መልካም ነው የሚል ምልከታዬን አስቀምጣለሁ እናንተም ሐሳባችሁን አጋሩኝ።