Get Mystery Box with random crypto!

ሶስቱ “ማንነቶቼ” (“የማንነትህ መለኪያ” ከተሰኘው የደ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ) ከስነ- | ሚሥጢሩ(The Secret)

ሶስቱ “ማንነቶቼ”
(“የማንነትህ መለኪያ” ከተሰኘው የደ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

ከስነ-ልቦና እይታ አንጻር ሶስት አይነት ማንነት እንዳሉን ማሰብ እንችላለን፡-

1. ራሴ “እንዲህ ነኝ” ብዬ የማስበው

እኔ በራሴ ላይ ያለኝ ተጽእኖ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ይህ ከሆነበት ምክንያቶች ዋነኛው ብዙውን ጊዜ ከራሴ ጋር ስለማሳልፍና ብዙ ነገሮችን ለራሴ የመናገር እድሉ ስላለኝ ነው፡፡ ይህ ልቀይረውና ሌላ አማራጭ ልፈልግለት የማልችለው እውነታ በመሆኑ በሚገባ ላስብበት ይገባኛል፡፡ በራሴ ላይ ያለኝ አመለካከት ራሴው በእኔው ላይ ከለጠፍኩበት ዋጋ አልፎ በመዝለቅ ወደ ትክክለኛው መስመር እስከሚገባ ድረስ ትክክለኛ መለኪያን እንዳላዳበርኩ አመልካች ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የሰውነቴ ዋጋ የማይለዋወጥ እንደሆነና እኔው በፈቃዴ ግን የተለያዩ የዋጋ ተመኖች እንዲለጠፉብኝ መፍቀድ እንደምችል ማስታወስ የግድ ነው፡፡

2. ሰዎችና ሁኔታዎች “እንዲህ ነህ” ብለው የሚነግሩኝ

ሰዎች ካለማቋረጥ መልእክትን ወደ እኛ ይልካሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቃል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሁኔታ፡፡ በተለይም የመደብ ልዩነት ከባህሉ ጋር ተገምዶ በሚገኝበት እንደኛው አይነት ማሕበረሰብ ውስጥ ጀርባችንን፣ የወቅቱ ሁኔታችንን፣ ያለንና የሌለንን በመደመርና በመቀነስ ካለማቋረጥ ማንነታችን ላይ ተመን ይለጥፋሉ፡፡ ይህ ዋጋ ደግሞ አንዴ ከፍ ይላል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ ይላል፡፡ ይህንን ሁኔታ በተገቢው ሚዛናዊነት የማስተናገዱ ግዴታ እኔው ላይ ነው ያለው፡፡ ሰዎች በእኔ ላይ የሚለጣጥፉት የዋጋ ውጣ ውረድ በማንነቴ ላይ ተጽእኖ የሚያመጣው እኔው ራሴ ስፈቅድለት ብቻ እንደሆነ ማስታወስ የግድ ነው፡፡

3. እውነተኛውና ትክክለኛው ማንነቴ

እውነተኛው ማንነቴ ማለት እኔው በራሴ ላይ ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች የለጠፉብኝ ተመን (Price) ሳይሆን ሰው በመሆኔ ከፈጣሪ የተሰጠኝ ዋጋ (Value) ነው፡፡ ይህ የመጨረሻ ስልጣን ያለውና ሁሉንም ትቼ ላምነው፣ ላሰላስለውና ልለማመደው የሚገባኝ እውነት ነው፡፡ ይህ የማንነቴ ዋጋ በምንም ሁኔታ ሊቀንስም ሆነ ሊጨምር አይችልም፡፡ ይህንን ዋጋ በጥረቴ ልጨምረውም ሆነ ላሳድገው አልችልም፡፡ ለዚያ ሊቀነስም ሆነ ሊጨመር ለማይችለው ከፈጣሪዬ ለተቀበልኩት የከበረ ዋጋ ላለው ማንነቴ የሚመጥን አመለካከትና የኑሮ ዘይቤ የመከተሌ ሁኔታ ግን የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡

እንግዲህ አንድ ሰው በራሱ ማንነት ላይ ያለው ዋጋ የተዛባ መሆኑን ለማወቅ ካሉን መመዘኛዎች መካከል አንዱ በችግሮቹ ላይ ያለውን አመለካከት በማጤን ነው፡፡ የተቃኘና ትክክለኛ ራስ-በራስ ምልከታ ያለው ሰው እለት በእለት በሚገጥመው ችግሩ ላይ ያለውም ምልከታ ሚዛናዊና አዎንታዊ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ችግር ሲገጥመው የወደቀ አመለካከት ያለው ሰው በቅድሚያ በራሱ ላይ ያለው አመለካከት አለመስተካከሉን አመልካች ነው፡፡

የኑሯችሁ ሁኔታ በተለዋወጠ ቁጥር በማንነታችሁ ላይ ያለችሁን አመለካከትና ለራሳችሁ የምትሰጡትን ግምት አትለዋውጡ፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብታልፉም የማንነታችሁ ዋጋ ያው ነው!

ድንቅ ቀን ተመኘሁላችሁ

@Abresh129
@the_law_of_attraction1