Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! #ዮሴፍ_አረጋዊ | ቅ/ማ/ዩኒቨርስቲ ግቢ ጉባዔ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
#ዮሴፍ_አረጋዊ
አረጋዊው ዮሴፍ ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ከቤተ ዳዊት ሲሆን እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰው የሚራራ ደግ ሰው ነበር፤ (ማቴ 1፥16-25 ፣ ሉቃ 1፥27)፡፡ ድግር ጠርቦ፣ ጥርብ አለዝቦ በመሸጥ ይተዳደር ነበር፤ ለዚህም ነው ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የጠራቢው ልጅ አይደለምን?›› እያሉ የሚጠሩት፤ (ማቴ 13፥55-56)፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ማርያምን (የቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ሐና እመ ማርያም እኅት) አግብቶ ያዕቆብ፣ ዮሳ፣ ስምዖን፣ ይሁዳና ሰሎሜ የሚባሉ ልጆችን ወልዷል፡፡ ሚስቱ ከሞተችበት በኋላ አይሁዳውያን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ በጠላትነት ተነሥተው ከቤተ መቅደስ ትውጣልን ባሉ ጊዜ ወስዶ ከቤቱ አስቀምጧታል፡፡ ከዚህ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በደስታዋም በኀዘኗም ጊዜ አልተለያትም፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደች ጊዜም ዳስ ሠርቶ አገልግሏታል፡፡
ሄሮድስ ሕፃናትን በሰይፍ በአስፈጀ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ለማዳን ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ በተሰደደች ጊዜ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ረሃቡን፣ ጥሙን፣ የቀን ሐሩሩን፣ የሌሊት ቁሩን ታግሣ በረሀ ለበረሀ በተንከራተተችበት ወቅት አልተለያትም፤ (ማቴ ምዕራፍ 2)፡፡
ከስደት ከተመለሱ በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አባት ሆኖ አሳድጎታል፤ አይሁዳውያን ጌታን የዮሴፍ ልጅ የሚሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከኒቆዲሞስ ጋር ገንዞ በአዲስ መቃብር አኑረውታል፤ (ዮሐ 19፥38)፡፡ አረጋዊው ዮሴፍ በ104 ዓመቱ ሐምሌ 26 ቀን ዐርፏል፡፡ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ጸጋና በረከት ይደርብን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ መጽሐፍ ቅዱስ