Get Mystery Box with random crypto!

ለመጸለይ ትጋት ላለመጸለይ ምክንያት ለሌለኝ ለእኔ ጸልዩልኝ! ━━━━━━━༺✞༻━━━━━━ በዲ | ቅድስት ፌብሮኒያ

ለመጸለይ ትጋት ላለመጸለይ ምክንያት ለሌለኝ ለእኔ ጸልዩልኝ!
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━

በዲያቆን ቴዎድሮስ በለጠ [በዕለተ-ልደቱ]

ሰው "የማትጸልየው ለምንድነው?" ሲባል ቀዳሚ መልሱ "ጊዜ ስለሌለኝ" የሚለው ነው። በጎውን መንገድ የሚያሳዩት ግን ይህን ይላሉ "የማንጸልየው ጊዜ ስለሌለን ሳይሆን ጊዜው የሌለን ስለማንጸልይ ነው!"

ምስጋናው ክቡር ልመናው ሥሙር የሆነለትማ ጸሎቱ ውኩፉ ኃጢዓቱ ግዱፍ ጊዜውም ትሩፍ ነው! ከሰዎች ጋር የሚያወራበትን ጊዜ የሚያሳጥር ፡ ከአምላኩ ጋር ለመነጋገር የሚጥር ሰው እንዴት ያለው "ዕድላም" ነው እናንተ! ከንግግሩ የሚቀንስ ከኃጢዓቱ ይቀንልና

☞ ወዘይጸልእ ብዙኃ ነቢበ ያሐጽጻ ለኃጢዓቱ ⇨ አብዝቶ መናገርን የሚጠላ ሰው ኃጢዓቱን ያሳንሳታል【ሲራ ፱፥፮】

የበረሐ አባቶችን ጥበብ የሚነግረን መጽሐፍ እንዲህ ስላለው ንግግር የመቀነስ ዝምታን የማብዛት ሕይወት የሚከተለውን አስተማሪ የቅዱስ አርሳንዮስ ታሪክ ያስቀምጣል።

ቅዱስ አርሳንዮስ ሁል ጊዜ ተሐራሚ ሆኖ በመዓልትና በሌሊት ይጸልይ ነበር:: ሰዎች ሲያነጋግሩት እንኳ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ላለማቋረጥ ጸጥ ይል ነበር:: ለዚህም በኣቱን ከገዳመ አስጤክስ አስር ምዕራፍ ያህል ርቆ ያለ ሲሆን አንድ ቀን አባ መቃርዮስ "ከእኛ ርቀህ የምትኖረው ስለምነው?" ቢለው "ለእኔስ ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት መኖር ባይቻለኝ ነው:: የእግዚአብሔር ፈቃድ አንዲት ስትሆን የሰው ፍፈቃዱ ግን ልዩ ልዩ ብዙም ነው"ብሎታል:: ሌሎችም አኃው ሄደው በአርምሞ እንዲህ ጸንቶ ስለመኖሩ ቢጠይቁት "I have often regretted the words I have spoken, but I have never regretted my silence ⇨ በተናገርኳቸው ቃላቶች ብዙ ጊዜ ተጸጽቼ አውቃለሁ፣ በዝምታዬ ግን በፍጹም ተጸጽቼ አላውቅም" አላቸው:: 【+ St. Arsenios the Great 】

ሰው ከሰው ጋር ከመጨዋወት እና አብሮ ከመኖር የራቀ ያህል ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመነጋገርና አንድ ለመሆን የበቃ ይሆናልና::

ጌታችንን በምናወድስበት ጸሎትም በልቡናው ንጽሕና ተወዳጅነቱ የተመሰከረለትን አበ ልሳናት ባህረ ጥበባት ቅዱስ ዮሐንስን የሚያነሳ ይህን እጅግ ጠቃሚ ተማጽኖ እናገኛለን ፦

ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዐሞ፣
ንጽሐ ሕሊናሁ ወልቡ ለዓይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ፣
ኢየሱስ ክርስቶስ መፍቀሬ የዋሃት እምተቀይሞ፣
ጸግወኒ ማዕፆ አፍ እንተ ይእቲ አርምሞ፣
ለትዕግሥትከ ከመ አእምር ዐቅሞ።

ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፤ ዮሐንስን ለሳመው መለኮታዊ አፍህ ሰላምታ ይገባል። የልቡናው ንጽሕና በፊትህ ተወዳጅነትን አግኝቷልና። ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤ ቅያሜ በአንተ ዘንድ ቦታ የለውም ቸርነት ግን የባሕርይህ ነው። ስለዚህ የትዕግሥትህን መጠን (ጥቅም) አውቅ ዘንድ። አፌም ክፉ ከመናገር ይቆጠብ ዘንድ የዝምታ ቁልፍ ስጠኝ።【መልክአ ኢየሱስ】

እንግዲህ በጎ ዘመን፡ መልካም ቀን፡ የተሻለ ጊዜ ለማየት አሁን ክፋትን እንቢኝ ተንኮልን ወዲያልኝ ብለን ብዙ እንጸልይ ብዙ ዝም እንበል፤ ባለቅኔው ሎሬት ከቆቃ የላኩትን ምክር እየሰማን እንደው ዝም ብለን እስኪ አብረን ዝም እንበል።

አብረን ዝም እንበል
·
·
·
ከሰው ኳኳታ እንነጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።【ጸጋዬ ገብረመድኅን 1961 ቆቃ。】

✧ "ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤" 【፩ጴጥ· ፫፥፲】

በመጨረሻውም መጨረሻ የምናገረው ነገር ቢኖር አለመናገርን ነው።

"አርምሞሰ ተፍፃሜተ ፍፃሜ ውእቱ" ይላል መጽሐፈ መነኮሳት፤ ይሔን ሁሉ ለመናገር ጊዜ የነበረኝ ለመጸለይ ግን ጊዜ አጠረኝ፤ ለመጸለይ ትጋት ላለመጸለይ ምክንያት ለሌለኝ ለእኔ ጸልዩልኝ! ◆ ክፍለ ሥላሴ

【 የማስታውሰው ፎቶው ገዳመ ቆሮንጦስ ጌታችን የጾመበትና የጸለየበት ታላቁ ሥፍራ የተነሳሁት ነው። ከመታወሻነቱ ባለፈ ወደ ሥዕሉ ዞሮ ለመጸለይ ጊዜ እንዳጠረኝ ከሥዕሉ ዞሮ ፎቶ ለመነሳት ግን በቂ ሠዓት እደነበረኝ አስታውሶኛል 】

————————————————————
በቴዎድሮስ በለጠ ⟟ ከደብረ ብርሃን [ በተወለድኩበት ቀን ነሐሴ ገብርኤል ፳፻፲፬ ዓ.ም ]
————————————————————