Get Mystery Box with random crypto!

ሶስቱ በፍጹም ልታፍሩባቸው የማይገባችሁ ነገሮች 1. በተፈጥሮ ባገኛችሁት ማንነታችሁ በፍጹም አትፈ | Art of motivation

ሶስቱ በፍጹም ልታፍሩባቸው የማይገባችሁ ነገሮች

1. በተፈጥሮ ባገኛችሁት ማንነታችሁ በፍጹም አትፈሩ! ዘራችሁ፣ ቋንቋችሁ፣ መልካችሁ፣ ቁመናችሁ፣ የተፈጥሮ ዝንባሌያችሁ፣ አእምሯችሁ ለመገንዘብ የሚቀናውና የማይቀናው . . . እና መሰል በፈጣሪ ምርጫ የተሰጧችሁ ነገሮች በፍጹም አያሳፍሩም፡፡ ማንነታችሁን ተቀበሉና ቀና ብላችሁ ኑሩ፡፡ እነዚህን ነገሮች ባለመሸሸግ ማንም ሰው አወቀውም ሆነ አላወቀው፣ እንዲሁም ደግሞ ማንም ሰው ምንም አለና አሰበ ምንም አይነት ስሜት የማይሰጣችሁ ደረጃ እስከምትደርሱ ድረስ በራሳችሁ ላይ ስሩ፡፡

2. በየእለቱ በሚሰማችሁ ስሜት በፍጹም አትፈሩ፡፡ስሜት ሁሉ ወደ ትክክለኛ ተግባር እንደማይወስድ የማወቃችንና ስሜትን ተከትሎ ለምናደርጋቸው ነገሮች የመጠንቀቃችን እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ በሚሰማን ስሜት ግን ልንሸማቀቅና ልናፍር አይገባም፡፡ የኃዘን ስሜት፣ የፍርሃት ስሜት፣ ግራ የመጋባት ስሜት፣ የመጸጸት ስሜትና የመሳሰሉት ስሜቶች ሰው የመሆናችንና በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የማለፋችን ማስረጃ ናቸው እንጂ በፍጹም ልናፍርባቸው የሚገቡ ነገሮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ፣ የሚሰማችሁን ስሜት ሳትደባብቁና ሳታምቁ በትክክለኛው ቦታ፣ ጊዜና መጠን የመግለጥን ነጻነት ለራሳችሁ ስጡ፡፡

3. በኑሮአችሁ ደረጃ በፍጹም አትፈሩ፡፡
ከገንዘብ፣ ከቁሳቁስና ከመሳሰሉት እዚህ ምድር ላይ ለቃቅመናቸው በመጨረሻም እዚሁ ጥለናቸው በምንሄዳቸው ነገሮች ላይ የተመሰረተ የማንነትን ዋጋ ተመን በራሳችሁ ላይ ላለማውጣት የምትችሉትን አድርጉ፡፡ ያላችሁበትን የኑሮ ደረጃ ሰዎች አወቁትም ሆነ አላወቁት በስሜታችሁና በስነ-ልቦናችሁ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እስከማያመጣ ድረስ ምልከታችሁን ለመቃኘት ሞክሩ፡፡

ሁላችንም ብንሆን ሊያሳፍረን የሚገባን ነገር የክፉ ባህሪያችን ጉዳይ፣ ሊያኮራን የሚገባን ነገር ደግሞ በማንነታችንና በአቅማችን የሰራነው መልካም ተግባር ጉዳይ መሆኑን የማስታወስ ውሎ ይሁንልን!

ዶ/ር እዮብ ማሞ