Get Mystery Box with random crypto!

ጭንቀትና ስነ ልቦናዊ መፍትሔው # ጭንቀት ምንድን ነው? ጭንቀት የሰውነትን ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚ | ስለ ጤና የቴሌግራም ቻናል 🔍💊💉

ጭንቀትና ስነ ልቦናዊ መፍትሔው

# ጭንቀት ምንድን ነው?
ጭንቀት የሰውነትን ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚያዛባ የአካል፣የአዕምሮና የስሜት ትንኮሳ(stimulus) የሚፈጥረው ምላሽ፣ ወይም የአንድ ሰው ፍላጎት (demand) ሊያንቀሳቅሰው ከሚችለው የግልና የማህበራዊ ሃብቶች አቅም በላይ ሆኖ ሲታየው የሚፈጠር ስሜት፣ ወይም ነገሮች ና ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን እንደወጡ ስናስብ የሚፈጠር ስሜት ነው፡፡

መጠኑና ጊዜው ይለያይ እንጂ ጭንቀት የማይነካው ሰው እንደሌላ ይታወቃል፡፡ በአንድ ወቀት በአንድ ኮሌጅ ውስጥ የሳይኮሎጂ ኮርስ ሳስተምር አንድ ተማሪ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣንን ጠቅሶ “እንዴት እሳቸው ይጨነቃሉ?” በማለት ሰውየው ከማንኛውም ጭንቀት በየትኛውም ሁኔታና ጊዜ ነፃ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ገልጾ እንደተሟገተ ትዝ ይለኛል፡፡

ሆኖም በየትኛውም የስልጣን እርከን ወይም የሥራ ሃላፊነት ላይ ብንሆን በጥቂቱም ቢሆን በተለያየ ጊዜና ሁኔታ ጭንቀት ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል፡፡ የሚወጡ ሳይንሳዊ መረጃዎች ደግሞ ሃላፊነትና ውሳኔ ሰጪነት ሲጨምር ጭንቀት እንደሚጨምር ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ነው ባለስልጣናት፣ ስራ አሰኪያጆች፣ ዲሬክተሮች፣ ሥራ ሃላፊዎች በጭንቀት መቆጣጠሪያ (stress management strategies) ስልቶች እንዲሰለጥኑ መደረግ ያለበት፡፡

በማንኛውም ደረጃ የሚሰራና ከስራ ውጪም የሆነ ሰው የጭንቀት መቆጣጠሪያ ስልቶችን መሰልጠኑ፤ማወቁና መተግበሩ የተረጋጋ ህይወት እንዲመራ ይረዳዋል፡፡ ጭንቀት ውሳኔን የማዛባትና ትኩረትን የመቀነስ ሃይል ስላለው የጭንቀት መቆጣጠሪያ ስልቶችን ማወቅና መሰልጠን ይገባቸዋል፡፡

#የጭንቀት ምንጮች ምንድን ናቸው?

የጭንቀት ምክኒያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ለይቶ ማየት ይቻላል፡- አካላዊና ስነ ልቦናዊ ምንጮች፡፡
እነዚህም የሚከተሉትን ሊያጠቃልል ይችላል፡-
• በስራ ቦታ በሚፈጠር የሥራ ጫና እና የሥራ አሰራር ግልፅነት ማጣት
• ከሚወዱት ሰው ጋር የሚፈጠር ችግር
• መሰረታዊ የኢኮኖሚ ግዴታዎችን መወጣት አለመቻል፡- ለምሳሌ የቤት ኪራይ፣ አስቤዛ፣ ወርሃዊ የመብራት ክፍያ ወዘተ…
• ለአዳዲስ ነገሮች አለመዘጋጀት፡- ለምሳሌ ልጅ መወለድ፣ አዲስን ስራ መያዝ
የትራፊክ መጨናነቅ
ከፍተኛ ድምፅ ህመም
• ከፍተኛ የአየር ሁኔታ፡- ለምሳሌ ከባድ ሙቀት ወይም ከባድ ቅዝቃዜ
• አካላዊ ህመም፣እንቅልፍ ማጣት፣ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ በሰውነት ላይ የሚፈጥሩት ጫና ወዘተ ናቸው
ቲምና ፔተርሰን (Timm and Peterson) የተባሉ ምሁራን በተለይ በሥራ አካባቢ የጭንቀት ምንጮች

የሚላቸውን እንደሚከተለው ይዘረዝራሉ።
ውጤታማ ያልሆነ ተግባቦት (Communications)
አግባብነት የጎደለው የመስሪያ ቤት አሰራር ከመጠን በላይ የሆነ የመረጃ ብዛት ወጥ ያልሆነ የሥራ አስኪያጆች ወይም የመሪዎች ባህሪ ከመጠን ያለፈ የስራ ብዛት ወይም ጫና አዲስ ሥራ መግባት የግል ችግሮች ጭንቀትን የሚዘሩ ግለሰቦች- በንግግራቸው ሁሉ ጭንቀት የሚፈጥር ወሬን የሚያወሩ (Stress carriers ይባላሉ)
የ ድርጅቶች ደሞዝ፣ፖሊሲ እና የስራ አካባቢ(working conditions)
የሥራ ቦታዎች ከፍተኛ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ፣ ከፍተኛ ብርሃን ወይም ድንግዝታ ለጭንቀት መነሻዎች እንደሆኑ በፃፉት መፅሃፍ ላይ ይገልፃሉ፡፡

#የጭንቀት ውጤቶች ምንድናቸው?
•የሰውነት ድካም
•ከፍተኛ የራስ ምታት
•ብስጭት
•የምግብ ፍላጎት መዛባት
•የማስታወስ ችሎታ መቀነስ
•ለራስ የሚሰጥ ዋጋ ወይም ክብር መቀነስ(low self-esteem)
•ከማህበራዊ ህይወት መገለል
•የ ደም ግፊት መጨመር
•ትንፋሽ ማጠር
•የወሲብ ፍላጎት መቀነስ
•የእንቅልፍ መዛባት
•የጨጓራና አንጀት ስርዓት መዛባት ወዘተ

ከእነዚህም በተጨማሪ ጭንቀት የልብ ህመምን፣ የቆዳ ችግርን(skin disorders) እና ሜታቦሊዝምን (በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ ኡደቶችን)የማዛባት አቅም አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም ለስነልቦናዊ ቀውሶች ለምሳሌ፡- ለፍርሃትና ለድብርት ይዳርጋል፡፡ ጭንቀት ስነልቦናዊ ችግር ነው ቢባልም አካላዊ ተፅእኖን ይፈጥራል፡፡

#ጭንቀትን ለመቀነስ ምን ማድረግ አለብን ?

ከላይ የተጠቀሱት ምሁራን ለጭንቀት መላ ይሆናሉ ያሉትን መፍትሄዎች እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፡-
ለአፍታ ዞር ይበሉ፡- ጭንቀት ከፈጠረብዎ ሁኔታ ወይም ሌላ ምንጭ ዞር ይበሉና የማሰቢያና የማሰላሰሊያ ጊዜ ይውሰዱ፡፡

ያውሩት፣ይናገሩት፡-ለቅርብና ለሚያምኑት ሰው የጭንቀትዎን ስሜት ይናገሩ፡፡ ባወሩ ቁጥር ይቀልልዎታል፡፡
ወጣ ብለው የሚወዱትን ይጫወቱ፡- የእግር ጉዞ ያድርጉ፣ ደረጃዎችን ወደ ላይና ወደ ታች ይውጡ፡፡
አንዳንዴ እጅ ይስጡ፡- ለምሳሌ እርስዎና ባለቤትዎ ወይም አለቃዎ “ይሄ ነው ትክክል ያኛው ነው ትክክል ” እያሉ ሙግት ከገቡና ጉዳዩ ብዙ ለወጥና ተፅዕኖ የማያመጣ ከሆነ ችላ ይበሉት፤ አንዳንዴ እያወቁ ይተውት፡፡

#ለሌሎች መልካም ነገር ያድርጉ፡-በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ሲገቡና ሃዘን ውስጥ ሲሆኑ ችግረኞችን በመርዳትና ልገሳ በማድረግ ይሳተፉ፤ ቀለል ይልልዎታል፡፡
በአንድ ጊዜ አንድን ነገር ይስሩ፡- ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለመስራት መሞከር ጭንቀትን ስለሚያባብስ እንደ ስራዎቹ ጠቃሚነትና አስቸኳይነት ቅደም ተከተል በማሲያዝ በአንድ ጊዜ አንድን ነገር ይስሩ፡፡

የታላቁን ሰው ፍላጎት አድብ ግዛ ይበሉት፡-አንዳንዴ የራስዎንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ችግር በሙሉ ራስዎ መፍታት እንደሚችሉ ማሰብዎ “በውስጥዎ ያለው የሃሰተኛው ትልቅ ሰው urge of superman” ምክር ነውና አድብ ግዛ ይበሉት፡፡ እርስዎ የሁሉንም ሰው ችግር ፈቺ አይደሉም !!

ትችትን መቋቋም ይለማመዱ፡- አንዳንድ ሰው ትንሽ ትችት እንቅልፍ ትነሳዋለች፡፡ በተጨማሪም ሌሎችንም ከመተቸት ይቆጠቡ። ቶማስ ፍሬድማን የ “ The world is flat” ፀሃፊ በዚህ አለም አንድ መንደር በሆነችበት ግሎባላይዜሽን ዘመን ለትችት ቆዳህን አወፍር (Make your skin thick) ብሎ ይመክራል፡፡
ለሌሎች ራስህን አስገኝ፡- ሰዎች ሲፈልጉህ ተገኝላቸው፡፡
#ብቸኝነት የጭንቀት ምክኒያትም ሊሆን ስለሚችል፡፡
ራስህን ለማዝናናት ጊዜ ውሰድ፡-ዘና ማለት፣መጫወት፣ አዳዲስ ነገሮችን መጎብኘት መንፈስን ያድሳል፣ ጭንቀትንም ይቀንሳል፡፡
ቆፍጣና ሁን፡- በቀን ወስጥ የምትሰራውን፣ የምትሄድበትን ሥፍራ፣ የምታገኘውን ሰው በትክክል ለይተህ በማወቅ ዝርክርክነትን አስወግድ።

መልካም ቀን !

ዶ/ር ዮናስ ላቀው
(ስነ አእምሮ ሀኪም (ሳይካያትሪስት))

ይህን መርጃ ለወዳጆ ያጋሩ ወደ " ሰለ ጤና " የቴሌግራም ቻናል ይጋብዙ! @seltena

ጤናማ ኢትዮጵያ (Healthy Ethiopia !)