Get Mystery Box with random crypto!

ጥራት እና ብዛት? ለባለትዳሮች . . . በፍቅር የመጀመሪያ ወራትና አልፎም በእጮኝነት ወራቶች | ስለ ጤና የቴሌግራም ቻናል 🔍💊💉

ጥራት እና ብዛት?
ለባለትዳሮች . . .

በፍቅር የመጀመሪያ ወራትና አልፎም በእጮኝነት ወራቶች ሁለት ፍቅረኛሞች ተገናኝተው አይጠግቡም፤ ሲገናኙም ትኩረታቸውን በሙሉ በፍቅረኛቸው ላይ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም ሲለያዩ እንደገና የሚገናኙበትን ቀን ይናፍቃሉ፡፡ ያም ሳያንስ በአካል ከተገናኙ በኋላ ሲለያዩ በስልክ እያወሩ ይሄዳሉ፡፡ እቤት ሲገቡም ሆነ በሌላ ቦታ ሆነው አብሮነቱን በማሕበራዊ ሚዲያ “ቻት” በማድረግ ይቀጥሉታል፡፡ ይህ “ጥራት” እና “ብዛት” ያለው ግንኙነት ከትዳር በኋላ የሚዘልቅላቸው ሰዎች ግን ቁጥራቸው ብዙ እንዳልሆነ ጥናትም ሆነ የግል ልምምድ ይነግረናል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ባልና ሚስት (እንዲሁም ከልጆች ጋር) ጥራት ያለው ጊዜ እስካሳለፉ ድረስ የሚገኛኙበትና አብረው የሚያሳልፉበት ጊዜ ብዙና ረጅም መሆን የለበትምነ ብለው ያስባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ባልና ሚስት ቤትም ሆነ ውጪ (ስራ፣ ንግድ …) ረጅም ጊዜ አብረው እስካሳለፉ ድረሰ ጥራት ምናምን የሚባል ነገር የለም ብለው ያስባሉ፡፡

እነዚህ ሁለት አብሮ የማሳለፍ ገጽታዎች የራሳቸው የሆነ ጥቅም ቢኖራቸውም በራሳቸው ብቻ ሙሉ እንዳልሆኑ ማሰብ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ባልና ሚስት ጤናማ የትዳር ግንኙነት የሚኖራቸው የቻሉትን ያህል አብረው ሲያሳልፉና ከዚያም በተጨማሪ አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ የእርስ-በርስ ትኩረት የሚሰጣጡበት ጥራት ያለው ሲሆን ነው፡፡

በብዛት ማሳለፍ ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል፡- በጊዜ እቤት መግባት፣ በትርፍ ጊዜ አብሮ መውጣትና መግባት፣ አብሮ ለመመገብም ሆነ ለመዝናናት ወጣ ማለትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

በጥራት ማሳለፍ ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል፡- አብረው ሲሆኑ ከማሕበራዊ መገናኛዎች መቆጠብ፣ እቤት ሲሆኑ ቴሌቪዥን የሚከፈትባቸውን ጊዜያት ሚዛናዊ ማድረግ፣ የውጪ ሰዎች ግርግር የማይበዛበት የቤት ውሎ ጊዜ ማዘጋጀት፣ መነጋገርና ማውራት እና የመሳሰሉት ይገኝበታል፡፡

ከትዳር አጋራችሁ ጋር የምታሳልፉትን ጊዜ ከብዛትና ከጥራት አንጻር ብትመዝኑት ከ10 ስንት ትሰጡታላችሁ?
እስቲ ከትዳር አጋራችሁ ጋር ጥራት ያለውን ጊዜ ወስኑና በዚህም ጉዳይ ላይ ተወያዩበት፡፡

#ምንጭ--->#ዶክተር እዮብ ማሞ #(የስነ ልቦና ሙሁር እና የ "25 ስኬት ቁልፎች "ደራሲ. ከዶክተር እዮብ ገፅ የተወሰደ ::