Get Mystery Box with random crypto!

የወደ ነገ ሂያጅ ነኝና ገጾች ሳሙኤል በለጠ የግጥም ጥፍሮች በዘፈቀደ አይባጥጡም። ገጣሚ የተለያ | ሳሙኤል በለጠ(ባማ)

የወደ ነገ ሂያጅ ነኝና ገጾች
ሳሙኤል በለጠ

የግጥም ጥፍሮች በዘፈቀደ አይባጥጡም። ገጣሚ የተለያየ ስሜት በልቡናው አለው በእርምጃ፣ በዕንባ፣ ወደ ውስጥ-ውስጡ ሲንቀሳቀስ ወይ ስሜቱ ሲለዋወጥ ግጥም ይፈጠራል። የተፈጠረው ግጥም ብዙ ያከራክራል። ሥነ-ውበቱ ጥሩ ነው? ወይስ? ቅርጹስ? ይዘቱስ? 'ሚለው ጥያቄ ያስነሳል።

በሩትገርስ ዩንቨርስቲ የሙዚቃ ጥናትና ፍልስፍና ፕሮፌሰር ነበሩት ፒተር ኬቪይ "በሥነ-ግጥም ውስጥ ያሉት ቅርጽና ይዘት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ይላሉ። በሌላ ጎራ ያሉ ምሁራን ደግሞ ግጥንም ግጥም የሚያሰኘው ቅርጹ ሳይሆን ይዘቱና ስሜቱ ነው። ይላሉ ይህን አጽንዖት እደግፋለሁ ምሳሌ

"..ከሐሩር ከቁር ማምለጫ
ጥጋት መሸሻ አጥተው
ከገንዳው የተተፈውን በልተው
ኅላዌን ትግል ሲገጥሙ
ላንተ ጮማ ምንህ ነው?
ይለኛል ያሾትለኛል
አዋዜው የልጆች ደም ነው፣
እንዴት ጣፈጠህ እያለ፣
ከሞራል ያካስሰኛል
ይለኛል፣ ሌላም ይለኛል።..."
[አበባው መላኩ 'ሙግት' ደቦ ገጽ-340]

ግጥሙ የቀረበበት ቅርጽ(Structure) ከዘለለታዊ የአገጣጠም ይትበሃል ያፈነገጠ ነው። ነገር ግን እጅግ ለስሜት ንክር ነው። ሥነ ግጥም ቅርጽ ፈጥሮ ሳይሆን የሚነሳው ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እንደሚሉት አንድ ሥነ- ግጥም ውበቱ የሚለካው በሚያስተላልፈው ሐሳብ ሳይሆን ሐሳብን ለመግለጽ በሚፈጥረው የቋንቋ ቅርጽ ነው።"[የወይራ ስር ጸሎት ገጽ xix] አስታወሰኝ ረጋሳ በአንድ መቶ ዘጠኝ ገጽ በሦስት መተላለፊያዎች በአርባ ሁለት ግጥሞች አዋቅሮ "ወደ ነገ ሒያጅ ነኝና" ብሎ 'ርዕስ ሸልሞት ለገበያ አብቅቶታል። የአስታወሰኝ ግጥሞች በጥልቅ እሳቤዎች፣ ቅጽብታዊ ንሽጣ(spontaneous impression)፣ በቅፅበታዊ ውስጣዊ ስሜት(immediate impression)
የተፈጠሩ ግጥሞች ናቸው። በምልከታም የቶሞሉ ጭምር:-

ከላይ የተጠቀሱ አይነት ግጥሞች ደግሞ ኀያሲ ዕዝራ አብደላ 'ተናዳፊ' ይላቸዋል። አጽንዖቱም  ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።" ይላል።

ፈገግ ብትል

ፈገግ ብትል አፋን ገልባ
የ ዓለም ፅልመት ረገፈች፣
ድንግል ኮኮብ ተሽኮርምማ
ከጥርሷ ላይ ተደገፈች፤

/ልጅቱ- እንደዚህ ናት ለሰው ደስታ/

ትወጣለች ማልዳ ቀድማ
የሳቅ መባ ልታበስር፤
እስኪመሽ ማን ያውቅና
ዕንባ እንዳለ ትራሷ ሥር፤

ብርሐን በቃኝ እግዜርዬ
ፍካት ፀሐይ አታብራልኝ፤
በዳመነ ሆዷ ታግባኝ
ልቧን ገልጠህ አራራልኝ፤

ዐይኗን አርገኝ በጨለማ
በቀን ሳቋ አታክንፈኝ፤
ከ ጥርሷ ጋር ውል የለኝም
ሐዘኗ ነው የለከፈኝ።

/ዕንባዋ ነው ያስለፈለፈኝ/
አስታወሰኝ ረጋሳ
[ወደ ነገ ሒያጅ ነኝና ገጽ 9-10]

በመጀመሪያው አንጓ እንደ ጠበል በማለዳ 'ሚጠጣ 'ውበት' ተሳለልን በሁለተኛው አንጓ በማለዳ 'ምትቃጠል(ምታቃጥለው አደረጋት) በመዝጊያው አርኬ አቆሰላት(ውበት ቆሰለ፣ ጣጣረ) የቆሰለው ውበት ኅልውናዬ ነው። አለን
ገጣሚ ምግባር ሲራጅ "የተከተልኳትን ያህል፤ መንገድ አለማለቁ...)" አንድ አንጓ አለው መሽቶ...(ማታ ሲሆን) ዕንባሽን ላባብል/ በውድቅት ሐዘን ሳካልል/ መጋኛ ነበር ያፅናናኝ/ የሰው ዘር ሕልሙ ላይ ሲስል። 'ሚል። ኮኮብ ዕንባ ጌጣጌጥ ፈገግታ በዕንባና በፈገግታ መኃል የኮኮብና የጌጣጌጥ ያህል ልዩነት አለ በኮኮብ(በዕንባ መመራት) ለኅላዌው አቅም ከሆነስ? የአስታወሰኝ ግጥም ሲኳጭ ይህን እውነት እናገኛለን።

["ወደ ነገ ሂያጅ ነኝና"] በሶስት ገጽ የተዋቀረ ግጥም ነው። የራሱ ሚዛን ከብዶታል የፀሐይን ጣዕም በጉዞው ለመቅመስ አልታደለም። ገጸ- ባህሪው ቆመና

''...ይልቅ ከንፈር አትምጠጡ
አልያም ለድል አንዳትዳሩኝ፤
ወደ...ነገ...ሂያጅ ነኝና
ጥቂት መንገድ አበድሩኝ።
አስታወሰኝ ረጋሳ
[ወደ ነገ ሒያጅ ነኝና ገጽ-82]

እውነት አለው ሰው ያራምዳል 'ንጂ መንገድ አያግዝም። ግን ሁሉ ይቀጥላል። ይህ ግጥም የአውስትራሊያዊውን ገጣሚ Rainer Maria Rilke አንድ ግጥም ያስታውሰናል።

Let everything happen to you
Beauty and terror
Just keep going
No feeling is final.
Rainer Maria Rilke
[The Poetry of Rilke]

( ሁሉ በአንተ ላይ ይሁን
ውበትና አመጽ በገላህ ቢፈራረቁም
ዝም ብለህ ቀጥል...
ምንም 'ስሜት' መጨረሻ አይደለም!
/ይቀጥላል/ )
ትርጉም ሳሙኤል በለጠ

አንጻረ-ዕይታ

ትል ከኛ ቢማርስ!

ቅዱስ ያሬድ

ከዘመን ባንድ ዕለት ጠሐይ ሲያቃጥለው፤
ካንድ ዛፍ ቢጋደም ጥላ እንዲያስጥለው

ግራ የገባው ትል
አቀበት ሊወጣ ቢታገል ከ ቅርፊት
ዕድል ደበለለው ከያሬድ እግር ፊት

ይህው ዛሬ ድረስ አባ እንደፈለጉት
አልገባቸው ሲለን ምሳሌ እያረጉት

"ሰው ተስፋ ካደረገ ለመሰኘት አንቱ
ከ እንሰሳ ይማራል እንኳንስ ከእናቱ
(ይሉናል)

እኔ ግን ከሁሉም
ጥያቄ አነሳለሁ እንደዚህ የምትል፤
"መሬት ሆኖ ኑሮው
ከዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ምን ፈለገ ያ ትል"!?

እኛም ታሪክ አለን
ስንት የተሸጋርን የመከራ እሳትን፤
ቢራቢሮ እስኪሆን
ትል ከሰው ቢማርስ ወድቆ መነሳትን።
አስታወሰኝ ረጋሳ
[ወደ ነገ ሒያጅ ነኝና ገጽ 28-29]

ደራሲና ኀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ
እንግሊዛዊው ደራሲ ሳሙኤል ጆንሰን ጠቅሶ እንዲህ ይላል። "የአንድ ጽሐፊ መማረኪያ ጉልበቶቹ ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም አዲስ ነገሮችን የተለመዱ ማድረግና የተለመዱትን አዲስ ማድረግ ናቸው።" አንድ ደራሲ ወይ ገጣሚ በዚህ ኪህሎቱ ይመዘናል። ምሳሌ

"...አንኳኩ ይከፈትላችዃል
ስትገቡ ሌላ በር ይጠብቃችዃል"

በዕውቀተ ሥዩም

መልሱ:-

አንኳኩ ይከፈታል።

ጥያቄው:-

በሩ የታል?

ሔኖክ በቀለ ለማ


አስታወሰኝ በዚህም ተሳክቶለታል። አዲስ ነገሮችን የተለመዱ እንዲሆኑ ስሜት ይሰጣቸዋል። የተለመዱትን ነገሮችን ደግሞ አዲስ ያደጋቸዋል። አስታወሰኝ ግጥም ሲያነብ ለግጥሞቹ 'ሚሰጣቸው ስሜትና ድምፅ እንዲሁም የአነባብ ለዛ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በቲክታክ ስሰማ መቼ ነው? ሲዲ የሚያወጣው ብዬ መናፈቄ አልቀረም!