Get Mystery Box with random crypto!

የመባረክ መንገድ መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ (ኤርምያስ 17:7) በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስ | Anteshe (Romans 11:36)

የመባረክ መንገድ
መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ
(ኤርምያስ 17:7)

በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ሚያዝያ 30 /2014 ዓ.ም የተካሄደው የእሁድ የጉባኤ የዝማሬ፣ የፀሎት ፣ አምልኮ እና የቃል ጊዜ
በዕለቱ በነበረው የቃል አገልግሎት መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ ያገለገሉ ሲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ኤርምያስ ምእራፍ 17 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሰረት በማድረግ "የመባረክ መንገድ" በሚል ርዕስ ቀጥለው በቀረቡት ነጥቦች ላይ አስተምረዋል።

መባረክ በእግዚአብሔር ፊት የስኬት ይሁንታ ማግኘት (ይሁንልህ መባል) ነው። በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ ስኬቱ የሚገለጠው በዋናነት በቁሳዊ መልክ ነበር። በማሕጸን ፍሬ፣ በጤንነትና፣ በብልጥግና መልክ ማለት ነው። ሰላምን (ደኀንነትንም) ይጨምራል (ዘዳ 7:15፣ 28:1-14)። ይህም እግዚአብሔርን በታማኝነት ከማምለክና ለእርሱ ከመታዘዝ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ጉዳይ ነው። የመግቢያው የንባብ ክፍላችን እንደዚህ ዓይነት በረከት የሚገኝበትን መንገድ ያሳያል።

ምዕራፉ የይሁዳ ሕዝብ የነበረበትን መንፈሳዊ ውድቀት በማውሳት ይጀምራል። ውድቀታቸው ጠለቅ ያለ ነበር። የእግዚአብሔር ሕግ ሊቀመጥበት በሚገባው የልባቸው ጽላት ኃጢአታቸው ተጽፎ ነበር። ኃጢአታቸው ለሕያው እግዚአብሔር የሚደረገውን ብቸኛና እውነተኛ አምልኮ በጣዖት አምልኮ የተካ ነበረ። ይህ ኃጢአት ወደ ቀጣዩም ትውልድ ዘልቆ ሊታሰብ የሚችል (አእምሯቸውን የሚይዝ) ሆኗል። የዚህ ኃጢአት ውጤት በእጃቸውና በደጃቸው የተቀመጠውን እግዚአብሔርን በረከት ሊያጡ የሚችሉበት ነበር።

"ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ... ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመ'በዝበዝ እሰጣለሁ" ይላል(17:3)። በዚህ ሃሳብ መነሻነት ቃሉ ስለ መባረክ መንገድ ሁለት ዓይነት ሰዎችን በማነጻጸር ያስተምረናል።
አንደኛው በሰው የሚታመን፣ ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፣ ልቡ ከእግዚአብሔር የሚመለስና "ርጉም" የተባለው ነው። ይህ ሰው፣ በምድረ በዳ እንዳለ ቁጥቋጦ፣ መልካምም በመጣ ጊዜ እንደማያይ፣ ሰው በሌለበት፣ ጨውም ባለበት፣ በምድረ በዳ፣ በደረቅ ሥፍራ እንደተቀመጠ ሰው ሆኖ ይታያል(17:5-6)።

ሁለተኛው ሰው፣ በእግዚአብሔር የታመነ፣ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነና "ቡሩክ" የተባለ ነው። ይህ ሰው፣ በውኃ አጠገብ በተተከለ፣ በወንዝም ዳር ሥሩን በሚዘረጋ፣ ሙቀትም ሲመጣ በማይፈራ፣ ቅጠሉም በሚለመልም፣ በድርቅ ዓመትም በማይሰጋ፣ ፍሬውም በማይቀቋረጥ ዛፍ ተመስሏል (17:7-8)። ንጽጽሩ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ አንድን ያስታውሰናል።

በዚህ የንባብ ክፍል ውሰጥ፣ የመባረክም ሆነ የመረገም(ያለመባረክ) መንገዱ በእግዚአብሔር ከመታመን ወይም ካለመታመን ጋር እንዴት እንደተያያዘ በግልጽ እንመለከታለን። በእግዚአብሔር መታመን፣ እርሱን ብቻ በታማኝነት በማምለክና ለእርሱ በመገዛት የሚገለጽ የጠራ አቋም ነው።

በአዲስ ኪዳን፣ መባረክ በክርስቶስ በኩል የሚገኝና በዓይነቱ ሰማያዊነትና መንፈሳዊነት ያለው ነው። ይኼኛው በረከት፣ ከዚያኛው የሚበልጥ ስለሆነ፣ ዋጋው እጅግ የላቀ ነው። "... በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም"(ሮሜ 8:1)። ይልቁንም፣ "በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በሰማያዊ ሥፍራ፣ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ" የተባረኩ ናቸው (ኤፌ1:3)።

እንግዲያውስ፣ ሰማያዊውን በረከት ከምድራዊው፣ መንፈሳዊውን በረከት ከቁሳዊውና ከአላፊው፣ መለየት ያስፈልገናል። ለመንፈሳዊውና ለዘላለማዊው በረከትም ዋጋ ልንሰጥ የገባናል። ለጊዜውም ቢሆን፣ ቁሳዊው ነገር ለምድራዊው ኑሯችን ሊያገለግለን እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር፣ ተጨማሪ እንጂ ዋና እንዲሆን፣ ቁሳዊውም ሀብት ቀልባችንን እንዲቆጣጠረው፣ በፍጹም መፍቀድ የለብንም። የእግዚአብሔር ቃል፣ "ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ" እንደሚላቸው እንደ "አንዳንዶች" እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባናል(1 ጢሞ 6:10)።

የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ቁሳዊ ብልጥግናዋን የምታውጅ፣ ክርስቶስን ግን ገፍታ ወደ ደጅ ያወጣች፣ በክርስቶስም ዓይን ምስኪንና ጎስቋላ ሆና የምትታይ ደሀና ዕውር ነበረች። ከእንደዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ጉስቁልና ሊያወጣንና እይታችንን ለመፈወስ ዛሬም ጌታ ጥሪውን ያቀርብልናል (ራዕ 3፣17-18)።
በሥጋ ለባሽም ሆነ በቁሳዊ ድጋፍ፣ ወይም በሌላ ነገር ተመክተን፣ በነፍሳችን ጠውላጋ ከመሆን፣ ሕይወት የለሽም ሆኖ ከመቅረት እንጠበቅ። ልባችን የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከሕያው አምላክ፣ ከእግዚአብሔር ወደ ኋላ አይመለስ። ከዳተኞች አንሁን። የእውነተኛና የዘላቂ በረከት መንገዱ፣ የዓለም መድኃኒት የሆነው፣ እኛንም ለማዳን በምትካችን ገብቶ የሞተው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ይህን በውል እንገንዘብ። ዘላለማዊውን በረከት ለመውረስ በክርስቶስ ላይ እንደገፍ። የሚስፈልገንን ሁሉ ራሱ ይሞላብናል። አኛ ግን ዋናውን ዋና እናድርግ። የመባረክም ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው።

ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች ትኩረት በመስጠትና በማብራራት በስብከታቸው መጨረሻ ለጉባኤው ፀሎት ተደርጎ የፕሮግራሙ ፍፃሜ ሆኗል፡፡

Follow Us
YouTube
https://is.gd/FGBCHawassaYoutube
Telegram
https://t.me/hawassafullgospelch
Facebook
https://facebook.com/FGBCHawassa

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ስነፅሁፍና ስነዳ አገልግሎት
ሚያዝያ 30 /2014 ዓ.ም