Get Mystery Box with random crypto!

[ጥር 22 ያረፈው የቅዱሳን መነኮሳት አባት የምንኩስና ጀማሪው የአባ እንጦንስ ድንቅ ተጋድሎ] | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

[ጥር 22 ያረፈው የቅዱሳን መነኮሳት አባት የምንኩስና ጀማሪው የአባ እንጦንስ ድንቅ ተጋድሎ]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
በረከቱ ይደርብንና የአባ እንጦንስን ታሪክ ከመጻፌ በፊት ከኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት አንዱ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምሆ ቅዱሳን መጽሐፉ ለአባ እንጦንስ ባቀረበው ሰላምታ እጀምራለሁ፦

“ሰላም ለአባ እንጦንስ ርእሶሙ ለመነኮሳት
ዘተውህቦ አስኬማ መላእክት
እንተ ለብስዋ ሐዋርያት፤
ኮከበ ሐቅል፤
ዘበጽሐ እስከ መስፈርተ አካል”፡፡
(እስከ መጠነ አካል የደረሰ የበረሓ ኮከብ ሐዋርያት የተጐናጸፏት የመላእክት አስኬማ የተሰጠው ለኾነ፤ ለርዕሰ መነኮሳት ለአባ እንጦንስ ሰላምታ ይገባል)

❖ የአባ እንጦንስ ወላጆቹ መልካም ክርስቲያን ነበሩና ከልጅነቱ ዠምሮ ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳድገውታል፤ በሰባት ዓመቱም የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን መማር ጀመረ፤ ያን ጊዜም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎናስ የዚኽ ብላቴና ክብር ተገልጾለት አስጠርቶ “ይኽ ሕፃን በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይኾናል፤ ዜናውም በዓለሙ ኹሉ ይወጣል” ብሎ ትንቢትን ተናግሮለት፤ ዲቁናን ሾመው፡፡

❖ ወላጆቹ ካረፉ ከሰባት ወር በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በልቡ ዐድሮ የሐዋርያትን ሕይወት ዘወትር ያስብ ነበር፤ ከዕለታት ባንዳቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ኺዶ ሳለ “ፍጹም ትኾን ዘንድ ከወደድኽ ኺድ ጥሪትኽን ኹሉ ሸጠኽ ለድኾች ስጥ በሰማይም ላንተ ድልብ አድርገው መጥተኽም ተከተለኝ” የሚለውን የወንጌልን ቃል ሲነበብ ሰማ (ሉቃ ፲፰፥፳፪)፤ በዚኽ ቅዱስ ቃል እግዚአብሔር ለርሱ እንደተናገረው በማሰብ፤ አባቱ የተወለትን ብዙ ሀብት ለድኾችና ለችግረኞች ሰጥቶ፤ እኅቱንም ወስዶ ከደናግል ገዳም አስገባት፡፡

❖ በዚያንም ወራት የምንኲስና ሥርዐት አልተገለጸም ነበርና እግዚአብሔርን ለማገልገል ከመንደር ወጣ ብሎ ብቻውን በመቀመጥ በጾም በጸሎት ተወስኖ መጋደል ዠመረ፤ በዚኽ ጊዜ አጋንንት ሌሊት ሕልምን በማሳየት በዝሙት ጾር የሚዋጉት ኾኑ፤ ከዚኽም በኋላ በባሕር ዳርቻ ወዳለች የመቃብር ቤት ኼዶ በተጋድሎ በረታ፤ አጋንንትም ቀንተው ታላቅ ድብደባን ደብድበው ጥለውት ቢኼዱም ጌታችን ግን አድኖታል፡፡

❖ ዳግመኛ ርሱን ለማስፈራራት በተለያዩ አራዊት በአንበሳ፣ በተኲላ፣ በእባብ፣ በጊንጥ ተመስለው ወደ ርሱ ሲመጡበት ቅዱስ እንጦንስ ግን ባደረበት የእግዚአብሔር ጸጋ “በእኔ ላይ ሥልጣን ካላችኊ እስቲ አሸንፉኝ” ብሎ ሲዘብትባቸው ወዲያውኑ እንደ ጢስ ተበትነው ጠፍተዋል፡፡ በዚኽ ዐይነት ተጋድሎ 20 ዓመታት ከኖረ በኋላ ከጌታ እንዲያስተምር ታዝዞ ብዙዎችን አስተምሮ በሃይማኖት አጸናቸው፡፡

❖ በሰማዕትነት ዘመን በዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ ወደ እስክንድርያ በመኼድ በሰማዕትነት ለመሞት ቢወጣም እነርሱ ግን በርሱ ላይ ምንም ምን እንዳያደርጉ አምላካዊ ኀይል ስለከለከለቻቸው ምንም ምን በርሱ ላይ ሊያደርጉበት አልቻሉም፤ ዘመነ ሰማዕታትም ካለፈ በኋላ አባ እንጦኒ ወደ ገዳሙ በመመለስ ማቅ በመልበስ ሕሙማንን እየፈወሰ በተጋድሎ ቆየ።

❖ ከዕለታት ባንዱ ቀን ከበዓቱ ውጣ ውጣ የሚል ፈተና ተነሥቶበት በማለዳ በትሩን ይዞ ከደጃፉ ላይ ቆመ፤ እንዳይቀር ጾሩ ትዝ ትዝ እያለው፤ እንዳይኼድ በዓቱ እየናፈቀው አንድ እግሩን ከውጪ አንድ እግሩን ከውስጥ አድርጎ ሲያወጣ ሲያወርድ መልአኩ የሰሌን ቀብ ደፍቶ፤ የሰሌን መቋረፊያ ለብሶ የሰሌን መታጠቂያ ታጥቆ ብትን ሰሌን ይዞ መጣ፤ ከዚያም ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸሎትን ሲያደርስ እንደገና ሰሌኑን ሲታታ፤ ከዚያም በየሰዓቱ እንዲኽ በማድረግ ሲጸልይ አሳይቶ “ኦ እንጦንዮስ ግበር ከመዝ ወአንተ ተአርፍ እምሀኬት ወእምጸብአ አጋንንት” (እንጦንዮስ ሆይ እንደዚኽ ሥራ አንተም ከስንፍና ከሰይጣናት ጦርነት ታርፋለኽ) ብሎ ሰጥቶታል፡፡

❖ ይኸም ምሳሌ ነው ቆቡ የአክሊለ ሦክ፤ ቀሚሱ የከለሜዳ ምሳሌ ነው፡፡

ዳግመኛም የብሉዩ ሊቃነ ካህናት በውስጥ እጀ ጠባብ በላይ እጀ ሰፊ በዚያ ላይ መጐናጸፊያ ይለብሳል፤ ከዚያ በላይ ደግሞ ከላይ እንደ መብርሂያት ያለ ይደርባል፤ ይኸነን ለብሶ አፍኣዊ መሥዋዕት ሠውቶ አፍኣዊ ኀጢአትን ያስተሰርይ ነበር፤ መነኰሳትም እንዲኽ ያለ ልብሰ ምንኲስና ለብሰው ውሳጣዊ መሥዋዕት ሠውተው ውሳጣዊ ኀጢአትን ያስተሰርያሉና።

በተጨማሪም እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ ኩፌት ደፍተው በሎታ ይዘው ዝናር ታጥቀው ጫማ አዝበው እንደወጡ መነኰሳትም እንዲኽ ያለ ልብሰ ምንኲስና ለብሰው በምናኔም ቢሉ በሞትም ከዚኽ ዓለም ይለያሉና፤ ሥጋውያን ዐርበኞችም ኲፌት አድርገው ዝናር ታጥቀው ጋሻ ጦር ይዘው ሥጋዊ ጠላታቸውን ድል ነሥተው የመጡ እንደኾነ ነገሥታት መኳንንት ካባ ላንቃ ያለብሷቸዋል መነኮሳትም ልብሰ ምንኲስና ረቂቅ ጠላታቸው ሰይጣንን በጾም በጸሎት በትሕርምት ድል የነሡ እንደኾነ ሥላሴ የብርሃን ካባ ላንቃ ያለብሷቸዋልና ፡፡

❖ ከዚያም በብዙ ተጋድሎ ኖሮ ከአባ ጳውሊ ጋር ተገናኝቶ አባ ጳውሊን ቀብሮ ከተመለሰ በኋላ በመጨረሻ ጌታችን ተገልጾለት በሰማያት ያለውን ክብር ነግሮት፤ መታሰቢያውን የሚያደርግ ለቤተ ክርስቲያን በስሙ መባ የሚሰጥ ኀጢአቱን ይቅር እንደሚልለትና ሥጋው የሚቀበርበት ገዳምም እጅግ ከፍ ከፍ እንደሚያደርግለት በውስጧም እንደ መላእክት የኾኑ ደጋጎች መነኮሳት እንዲኖሩባት እንደሚያደርግለት እጅግ ብዙ ቃል ኪዳንን ሰጥቶት ዐረገ።

❖ አባ እንጦኒም እጅጉን ደስ ብሎታል፤ ከዚያም ለደቀ መዝሙሩ ለአባ መቃርስ አስኬማንና የምንኲስና ልብስን አለበሰው፤ ዕረፍቱም እንደቀረበ ባወቀ ጊዜ በትሩን ለልጁ ለአባ መቃርስ፣ ምንጣፉን ለሊቁ አትናቴዎስ፣ የፍየል ሌጦ ዐጽፉን ለመንፈስ ልጁ ለኤጲስ ቆጶሱ ለአባ ሰራብዮን እንዲሰጡ ልጆቹን አዝዞ በ120 ዓመቱ ጥር 22 ጋደም እንዳለ ነፍሱ በይባቤ መላእክት፣ በመዐዛ ገነት ተለይታለች፡፡የአባ እንጦንስን የተጋድሎ ታሪክ የጻፈው ታላቁ ሊቅ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ ነው።

❖ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አርከ ሥሉስም የአባ እንጦንስን ተጋድሎ በዐርኬው፡-
“ሰላም ለብሕታዌሁ እንበለ ሕጸጽ ወንትጋ
ውስተ ናሕስ ከመ ዖፍ ወበቤት አምሳለ ጉጋ
ብእሴ ሰማይ እንጦኒ ወመልአከ ምድር በጸጋ
ለቤተ ብለኔ እንዘ ይሜንን ሕጋ
መዋዕለ ሕይወቱ ኢተኀጽበ ሥጋ”
(ያለፍጹም ጒድለት ለብቸኝነቱ ሰላምታ ይገባል፤ እንደ ዎፍ በሰገነት እንደ ጒጒት (ቊንጫ) በቤት ውስጥ ኾኖ፤ በጸጋ የምድር መልአክና የሰማይ ሰው የኾነ እንጦኒ የመታጠቢያ ቤት ሕጓን እየናቀ መላ ዘመኑን አካሉን አልታጠበም) በማለት ጽኑ ተጋድሎውን መስክሮለታል፡፡

[አበ መነኮሳት ወላዴ አእላፍ የበረሐው ኮከብ ቅዱስ አባ እንጦንስ ሆይ በረከትኽን አሳድርብኝ፤ ቅድስት ጸሎትኽም ዘወትር ትርዳኝ]
አባ እንጦንስ የጸለዩበት አስደናቂ ዋሻን በዚህ የYoutube ሊንክ ይመልከቱ



ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
(በአስተያየት መስጫው ላይ በረከቱን ትሳተፉ ዘንድ ታላቁን አባት ቅዱስ እንጦንስን አመስግኑት)