Get Mystery Box with random crypto!

የኖኅ መርከብ በኪንታኪ (በዶክተር ሮዳስ ታደሰ) በሕይወቴ ደስ ካሰኙኝ ጉዞዎች ምድቡ የሆነውና | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

የኖኅ መርከብ በኪንታኪ (በዶክተር ሮዳስ ታደሰ)
በሕይወቴ ደስ ካሰኙኝ ጉዞዎች ምድቡ የሆነውና 5000 ዓመት ወደ ኋላ የመለሰኝ ጉብኝቴ በሰሜን አሜሪካ ኪንታኪ የሚገኘው በኖኅ መርከብ አምሳል የተሠራውን 102 ሚሊየን ደላር የፈጀውን ግዙፍ መርከብን ግንቦት 30/ 2015 ዓ.ም.  መጎብኘቴ ነበር።

ዛሬ ከሌሊቱ 9 ሰዓት (3 AM) ላይ ዲያቆን ዐማኑኤል ቤት ከመጣ በኋላ ወንድማዊ ሰላምታ ተሰጣጥተን ወደ መኪናው ገባን ከዚያም 527.3 mi ወይም 848.607 ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ ጸሎታችንን አደረግን።

እጅግ የሚያስደስቱ ከኖኅ መርከብ አሠራር ጋር የተያያዙ ቀመሮችን እያወጋን ለ9 ሰዓቶች ያለምንም እንቅልፍ ጉዟችንን እጅግ የተፈጥሮ መስሕቦችን የለመለሙ ዕፅዋትን እያየን ይልቁን የፀሐይን ደማቅ አወጣጧን በምሥራቅ አድማስ እያደነቅን ቨርጂንያን ሜሪላንድን ፔንሲሊቫንያን ዌስት ቨርጂንያን ኦሀዮን ተጉዘን ኪንታኪ ገባን።

ከዚያም እጅግ ወደጓጓኹበት የኖኅ መርከብ አምሳል ወደተሠራው ቦታ አመራን ግዙፉ መርከብ ከሩቅ ይጣራል ወደግቢው ስንጠጋ መርከቡን የሚጎበኘው የሀገር ጎብኚ በተንጣለለው ግቢ ተገኝቷል።
የኖኅ መርከብ ውክልና ያለው ይኽ መርከብ ርዝመቱ 510 ጫማ (155 ሜ)፣ ስፋቱ 85 ጫማ (26 ሜ) እና ቁመቱ 51 ጫማ (16 ሜ) አለው።
መርከቡ እያንዳንዳቸው 18 ጫማ (5.5 ሜትር) ቁመት ያላቸው በኖኅ መርከብ አምሳል በሦስት ፎቅ የተደረደሩ 132 በመርከቡ ይኖሩ የነበሩ ማሳያዎችን ይዟል። በውስጡ የሚሰማው ድምፀ አራዊት የወፎች ጩኸት በእጅጉ ያስገርማል። የኖኅን ታሪክ የጥፋት ውሃን በዝርዝር የሚያሳዩት በጥንቃቄ የተቀመጡት እያንዳንዱ የመርከቡ ክፍሎች በዐይን ካልኾነ በቀር ጽሑፍ ለመግለጽ ቃላት ያንስበታል።
በእጅጉ የደነቀኝ በመርከቡ ውስጥ ካሉት የሚጎበኙ ክፍሎች የመጀመሪያው 'ኢትዮጵያ" ተብሎ የተጻፈበት ክፍል ሲኾን የኢትዮጵያዊው ጀንደረባ ታሪክና የኢትዮጵያ ጥንታዊ መስቀል በቦታው ይገኛል። ከዚያም ጥቂት ሀገራት ብቻ ስማቸው ተጽፏል።
ይህንንና ሌላውን ጉብኝት በአድናቆት ከጎበኘሁ በኋላ ከዲያቆን ዐማኑኤል ጋር ወደ 3D ክፍል በመግባት መነጽር ከተደረገልን በኋላ በቨርቹአል ሪአሊት ወደ ኖኅ ዘመን ተጓዝን፣ አስፈሪም አስደሳችም የኖኅ ዘመን ክስተቶችን ኹሉ አይተን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ምናርፍበት ቦታ ጉዞ በማድረግ ላይ እያለን በመኪናው ውስጥ ሳለሁ ለማስታወሻነት ጻፍኩት። በሀገሬም ቢኖር ብዬ መልካም ምኞትን ተመኘሁ። የቀረጽኩትንም በ YouTube ላይ ሰሞኑን እንደማጋራችሁ ተስፋ አለኝ።