Get Mystery Box with random crypto!

ከናፈኳቸው ጓደኞቼ ጋር ዛሬ ኀሙስ ያሳለፍኩ ምርጥ ምሽት ለረጅም ጊዜ በሚጥለው ዝናብ በጉም ተሸፍኖ | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

ከናፈኳቸው ጓደኞቼ ጋር ዛሬ ኀሙስ ያሳለፍኩ ምርጥ ምሽት ለረጅም ጊዜ በሚጥለው ዝናብ በጉም ተሸፍኖ የነበረው የዐዲስ አበባ ሰማይ ዛሬ ዝናብ ባለመጣሉ ሰማዩ ጥርት በማለቱ የምሽት ሰማያዊ ጓደኞቼን በብቸኝነቴ ብቻዬን በማግኘቴ ምሽቴን የበለጠ አስደሳች አርጎልኛል።
ይኸውም የሰማይ መመልከቻዎቼን በመያዝ ዐይኖቼን ወደ ሰማይ ሳቀና፦
ከተወለደች 7 ቀን የሞላት 41% የምታበራዋ ተወዳጇ የዛሬዋ ጨረቃ ላይ ዐይኖቼ ተተከሉ። ጉድጓዶቿ ናፍቀውኝ ነበረና በቴሌስኮፔ እስኪበቃኝ አየኋት።
ዐይኖቼ ፕላኔት ለማየት ናፍቀዋልና ውቧ ዕለተ ዐርብን የምትመግብ ዝሁራ (ፕላኔት ቬኑስ) ከጨረቃ አጠገብ ከመንታዎቹ ካስቶርና ወንድሙ ፓሉክስ ውስጥ ተሸጉጣ ነበር። በጎኗ ደግሞ የማግሰኞ መጋቢ ጦረኛዋ ቀዩ ፕላኔት ማርስ ነበርና በፍቅር ዐይኖቼ ርሱ ላይ ተተከሉ። ያው ማርስ የቅዱስ ሚካኤል ምሳሌነቱን ስለማውቀው በእጅጉ የምረዳው ምስጢራቸውና ታሪካቸውን በማመላለስ ውስጤን በጥበብ አስደሰትኩ።

ፍንትው ባለው የዛሬው ሰማይ መቼም ዞዲያክ ሰማዩ ላይ ይዋኛሉ። ወደ ምሥራቅ ስመለከት ከአድማሱ ከፍ ብሎ ሚዛን ሊብራን፤ ከፍ ብላ ሰንቡላ ቪርጎ የስንዴ ዛላዋን ይዛ፤ በመቀጠል አንበሳው አሰድ፤ በመቀጠል ሸርጣን ካንሰር፤ ቬኑስ አጠገብ ደግሞ ጥንዶቹ ጀሚናይ ፏፏ ብለው ይታዩ ነበርና የከዋክብቱን ስሞች ለብቻዬ በተመስጦ ብቻዬን እየጠራሁ ፈጣሪ ለምን እንደሠራቸው በሚገባ እረዳለሁና በምናብ ጥቂት ወግን ከዞዲያክ ጋር ተነጋገርኩ። አይ እናንተ ዞዲያክ የያዛችሁትን ምስጢር ሰው ቢረዳ ኖሮ ዐይኖቹን ከእናንተ መቼ ይነቅል ነበር።

የመጨረሻ ጓደኞቼ ሕብራተ ከዋክብት ናቸውን ወደ ሰሜን ስዞር ድቡ ኡርሳ ሜጀርን በሰማይ ላይ ከነጭራው ተዘርግቶ አየሁት።
በደቡብ አልፋ ሴንቹአሪን የያዘውን ቀስተኛውን ሴንታውረስን፤ የኖኅ መርከብ ካሪናን፤ ኖኀ የላካት ርግብ ኮሉምባ በአፏ የወይራ ቀንበጧን ይዛ ስትበር አይቼ ታሪኩን አመላለስኩ፤ ከዚያም የደቡብ መስቀል አብርቶ አየሁ።
የደቡብ ሰማይ ምስጢሩ ድንቅ ነውና አስፈሪ ነገር ላይ በድንገት ዐይኖቼ ተተከሉ ይኸውም የእሳት ምድጃ (የገሃነም) ምሳሌ የሚኾነው ክራተር ሕብረ ኮከብ በወደቀው እባብ ሀይድራ ጀርባ ላይ ሲፈስ ተመልክቼ በመገረም እያንዳንዱን ኮከብ ከነስማቸው ከነትርጉማቸው ካመላለስኩ በኋላ ወደ ምሥራቅ ስመለስ ኮከብ ቦኤቲስ ከነማጨዱ አየሁት። ወደ ምሥራቅ አሻግሬ ስመለከት የዐባይ ኮከብ ሳይረስን በሩቁ በማየቴ ውስጤ በደመና ተመልቶ በመጨረሻም በዓለመ ከዋክብት ውስጥ ድንቅ ምስጢርን ያስቀመጠ ለወደዱት ብቻ የሚገልጸውን የፍጥረታት ፈጣሪ አምላኬን አመሰገንኩ።
(18/09/2015 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ ሰማይ ሥር መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)