Get Mystery Box with random crypto!

የምትጠይቀው አላጣህም! ፨፨፨፨፨፨//////////፨፨፨፨፨፨ የልብህን መሻት፣ የውስጥህን ፍላጎት፣ | ቀና~ትውልድ

የምትጠይቀው አላጣህም!
፨፨፨፨፨፨//////////፨፨፨፨፨፨
የልብህን መሻት፣ የውስጥህን ፍላጎት፣ አምሮትህን በለየህ ማግስት ለጥያቄ ትዘጋጃለህ። ያሰብከው ይሆንልህ ዘንድ፣ የተመኘሀው ይፈፀምልህ ዘንድ ለተማፅኖ፣ ለጥያቄ፣ ለልመና ትሰናዳለህ። ጠያቂ ነህና ተጠያቂ ያስፈልግሃል፤ የምትማፀን ነህና የምትማፀነው ያስፈልግሃል። የጥያቄህ ርቀትና ግዝፈት ዋናው መፅዋችና ሰጪ ጋር እንድትሔድ ሊያስገድድህ ይችላል። መሔድህ ችግር የለውም እምነትህ ግን ችግር ሲፈጥር ትመለከታለህ። የጥያቄህ ምላሽ ምንም ይሁን ምን ምላሽ ተብሎ እስከተሰጠህ ወይም ምላሽ መሆኑን እስከተረዳህ ድረስ በፀጋ የመቀበል ግዴታ ይኖርብሃል።

አዎ! ጀግናዬ..! የምትጠይቀው አላጣህም፤ የምትማፀነው፣ የምታለቅስበት አካል አላጣህም። ሰው ፊት ከማልቀስ በላይ አምላክ ፊት የፈሰሰ እንባ ያልጠበከውንም ክፍተትህን ይሞላልሃል፤ ለመጠየቅ ያፈርከውን ጥያቄ ይመልስልሃል። ቅርበትህና እምነትህ ብቻ ያንን የችግር ባህር፣ የሰቆቃ መዓት ያሻግርሃል። እራስህን ለሰው ማሳየት ከጀመርክ፣ ሚስጥርህን ማካፈል ከጀመርክ ለረጅም ጊዜ ቆይተሃል፤ ሰዎችን በመቀየር ብዙ ለፍተሃል፤ ሸክምህን ያቀሉልህ ዘንድ ሁነኛ የምትላቸውን ወዳጆች ቀርበሃል ነገር ግን ያሰብከውን ምላሽ አላገኘህም፤ በእነርሱ ላይም ቢሆን አድሮ የሚያግዝህ፣ የሚያሳርፍህ የሸሸሀው ፈጣሪህ እንደሆነ ዘንግተሃል።

አዎ! ለጥያቄህ ምላሽ፣ ለችግርህ መፍቴ፣ ለጭንቀትህ እረፍት ፍለጋ ወደ አምላክህ መቅረብህ በእራሱ እምነትህን በጥቂቱ ያሳይ ይሆናል እንጂ በፍጡም በቂ አይደለም። ከሰዎች የምትጠብቀውና ከአምላክ የምትጠብቀው ምላሽ ለዩነቱ ሰው ይስታል፣ ያጎድላል፤ አምላክ ግን አይስትም፣ አያጎድልም፤ የምላሹ ፍፁምነት አጠያያቂ ሆኖ አያውቅም። እናም የምትጠይቀውና የምታወያየው ባላጣህበት አኳሃን ያለህን ሚስጥር ሁሉ ለሰው ለመናር አትቸኩል፤ በሰዎች መጠቋቆሚያ ለመሆን አትጣደፍ። ጉዳይህን ባትነገረውም የሚያውቀው አምላክ አለና ከእርሱ ሁሉን ከሚያውቀው በላይ መፍትሔ ፍለጋ ሌላ ቦታ መሔድህም ሌላ ጥያቄ እንዳያስነሳብህ፣ ከመንገድ እንዳያስትህ ተጠንቀቅ። ምንም ብትጠይቅ የማይታዘብህ፣ የማይፈርድብህ ፈጣሪ እያለህ እንኳን ተናግረህ፣ ታሪክህን አውጥተህ ይቅርና ባልሆንከውና ባልተናገርከው ነገር ስም ከሚያወጣልህንና ፍርድን ከሚበይንብህ ሰው እራስህን ግታ፣ እራስህን ጠብቅ። በእርግጥም የጥያቄህን ትክክለኛ ምላሽ ከፈለክ አምላክህን በእምነት ጠይቅ

ውብ ቀን ይሁንልን!
ምክረ-አዕምሮ