Get Mystery Box with random crypto!

አንድ ፂሙን ያጎፈረ ስከርፉን ያጣፋ ደራሲ ፈላስፋ ከዚህ ሀገር ሰዎች ራሱን ለይቶ በቅኔ በቋንቋ | የኔ' ማስታወሻ ...✍️

አንድ
ፂሙን ያጎፈረ ስከርፉን ያጣፋ
ደራሲ ፈላስፋ
ከዚህ ሀገር ሰዎች ራሱን ለይቶ
በቅኔ በቋንቋ ሚስጥር አበራይቶ
ያየውን ጎዳና መንገድ አመላክቶ
አረቄ ይጠጣል ከሀሳቡ ባነሱ መንጋ ተበሳጭቶ!
ሲጋራውን ለኮስ...አረጌውን ብድግ
ይሄ ስብስብ መንጋ ለምን ነው 'ማያድግ?
ለምን አያነብም መፅሄት ጋዜጣ?
መነሳት መራመድ መፏለል ዝነጣ.. .
ለምን አያነብም ... አዲስ ፍልስፍና?
ለምን አይመሰጥም.. .በግጥም ትወና?
መነሳት መተኛት ተመሳሳይ ዑደት
ያበሳጫል እውነት!
ሲጋራውን ለኮስ የጫት ቅጠል ቅንጥስ
ቃም ቃም ... ቃም ቃም ...
እንዴት አንድ ይጠፋል ከዚህ መንጋ ልባም?
መነሳት መተኛት.. ስራ መሄድ ትዳር
ሁሌ አንድ መንገድ ... መፍዙዝ የቁም ስካር
እንዴት አይጠይቅም ፈጣሪን ሞግቶ?
ለምን አይመሰጥም መፅሀፍ ሸምቶ ?
እከሌ ተወልዶ በዚህ ዓመት ሞተ
ታሪክ ሳያስቀምጥ ስሙን ሳያስነሳ ...
አላወቀም እንጂ ኖሮም ነው ሬሳ !
ለምን አያነብም ... አዲስ ፍልስፍና?
ለምን አይመሰጥም.. .በግጥም ትወና?
ሁሌ የስጋ መንገድ ተመሳሳይ ዑደት
ያበሳጫል እውነት!
ብሎ ይናደዳል መሸታ ቤት ገብቶ
ሲጋራ እያጨሰ አረቄ ጠጥቶ ...

ፂሙን ያጎፈረ ስከርፉን ያጣፋ
ደራሲ ፈላስፋ
ምናለ ቢሰማ መንጋው የሚለውን
ስለሱ ያየውን ...
አይታጠብ አይፀዳ ፂሙን አይከላ
መፅሀፍ ታቅፎ አዋቂ ነኝ ይላል
የሰፈር ቀውላላ ...
ምናለ ቢታጠብ.. . ራሱን ቢጠብቅ?
ምናለ ቢያገባ.. .ልጆቹን ቢያሳድግ ?
ምናለ ቢሰራ ... ከሚጫጭር ግጥም?
እንዲህ ለቅፈላ ... ሰንፎ ከሚለግም !
አሁን ምን ያደርጋል ?
አዋቂ ነኝ ማለት ... መደስኮር መደንፋት
ሳይፀዱ ሳያምሩ
አሁን ምን ያደርጋል ?
ላልኖሩበት ዓለም ታሪክን ቢያስቀሩ ።
አሁን ምን ያደርጋል ?
ራሱን የማያቅ ያ ግብዝ ፈላስፋ
ሌላውን ለማወቅ ቢጫጭር ቢለፋ?
ለምን ስራ አይሰራም ... ኑሮው እንዲቃና?
ለምን አይመሰጥም.. .በልጁ አንገት ቃና?
አረቄ መጠጣት ሲጋራ መጠጣት
መፅሀፍ ይዞ መዞር ... ተመሳሳይ ዑደት
ያበሳጫል እውነት!

(ሚካኤል.አ)

@poethaymi