2024-04-19 13:09:58
ለምን ተፈጠርኩ? ለምን እኖራለሁ? የሕይወቴ ትርጉምስ ምንድን ነው።
አብዘርዲዝም - ካምዩ
መጠለያ ባጣህበት ሁኔታ በዝናብ እየተደበደብክ እየተጓዝክ ሳለ፣ መሳቅ ጀምረህ አታውቅም? የሆነ ጉዳይ በእጅጉ ተበላሽቶብህ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ አይነት ስሜት ፈገግ ብለህ አታውቅም? በችግሮችህ ውስጥ ሳለህ እያንዳንዷን ደቂቃ ወደህ አታውቅም? ይህን አልበርት ካምዩ አብሰርዲቲ ይለዋል፡፡
ካምዩ ፈረንሳያዊ የኤግዚስታንሻሊዝም (ህላዌነት) ፈላስፋ ነው፡፡ በቀላል ታሪክም ፍልስፍናውን ይጀምራል፡፡
ሲሲፈስ የተባለ የጥንታዊቷ ግሪክ ንጉስ አማልክቱን የሚያስቆጣ ተግባር ፈጸመ። ሲሲፈስ ሞትን በሰንሰለት አሰረው፡፡ ይህንንም በማድረጉ የሰው ልጅ ዘላለም ኗሪ ሆነ። በመጨረሻም አማልክቱ ሲሲፈስ ያደረገውን አወቁ፤ በርሱ ላይም ዘላለማዊ ቅጣት ፈረዱበት፤ የሞትንም ሰንሰለት በጠሱ፡፡ እናም ሲሲፈስ ለመቀጣጫ እንዲሆነው ዘላለም ድንጋይ ሲያንከባልል እንዲኖር ተፈረደበት። ግዙፍ ቋጥኝ እየገፋ ወደ ተራራ አናት ያደርስዋል፤ ወዲያውም ቋጥኙ ወደ ተራራው ስር ተንከባሎ ይወርዳል፤ ሲሲፈስም እንደገና ከታች ጀምሮ ወደ ላይ ቋጥኙን ይገፋዋል፡፡ ቋጥኙም ተመልሶ ወደ ተራራው ግርጌ ይወርዳል...
ይህ የሲሲፈስ ዘላለማዊ ቅጣቱ ነው። ያንተስ ሕይወት ከርሱ ይለያልን? የሲሲፈስ እልፍ ጊዜ እየተመላለሰ ቋጥኝ ማንከባለሉ ትርጉም አልባ እንደሆነ ይሰማሃል? ሆኖም ያንተ ሕይወት ትርጓሜው ምንድን ነው?
ሕይወትህን ልክ እንደ ሲሲፈስ ትርጉም አልባ ቋጥኞችን ስትገፋ ነው የምታሳልፈው፡፡ የማይሞላ ሆድ አለህ... ሚልዮን ጊዜ መግበኸው ሚልዮን ጊዜ ጎድሎብሃል፤ የማይሞላ ፍላጎት አለ... ሚልዮን ጊዜ ተደስተህ ሚልዮን ጊዜም ተከፍተሃል። በጠዋት ከእንቅልፍህ ትነሳለህ፤ ገንዘብን ፍለጋም ወደ ስራ ትሄዳለህ... ቀኑ ይመሻል ዳግም ይነጋል... በጥዋት ወደ ስራ ትሄዳለህ. ከእለታት በአንዱ ቀንም ራስህን በሞት አልጋ ላይ ታገኘዋለህ፡፡ እናም በሕይወት ዘመንህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ልክ እንደ ሲሲፈስ ቋጥኝ መግፋት- ዘበት ነው!
የሰው ልጅ ህልቆ መሳፍርት በሌለው ሁለንተና ላይ ራሱን ሲያገኘው፤ “ለምን?” የሚል ጥያቄን ይጠይቃል። ለምን ተፈጠርኩ? ለምን እኖራለሁ? የሕይወቴ ትርጉምስ ምንድን ነው? ሆኖም እውነታው ይህ ነው... ያንተም የኔም የመኖር ሁኔታ በአጋጣሚዎች የተፈጠረ እንጂ ትርጓሜ ያለው ነገር አይደለም በጸጥታ ውስጥ ባለው በግዙፉ ሁለንተና ውስጥ አንተ ማን ነህና ሕይወትህ ትርጉም ይኖረዋል? ሁለንተናም ስላንተ ግድ የለውም... ለጥያቄህም መልስ የለውም፡፡ ሆኖም ይህ መሆኑን ብናውቅም፤ ሰው ነንና የሕይወታችንን ትርጉም መፈለጋችንን አናቆምም የሞትን ቀን ያበቃለታል። ሞት በሕይወታችን የኖርንላቸውን ተግባራቶች በሙሉ ዋጋ ያሳጣቸዋል፡፡ ይህንን ነው አብሰርዲዝም ወይም የሕይወት ዘበትነት ሲል የሚጠራው፡፡
እና ዘበት በሆነ ዓለም ላይ እንዴት እንኑር?
ታይታኒክ በተባለው ፊልም መጨረሻ ላይ መርከቧ እየሰመጠች ሳለ ሙዚቀኞች ቫዮሊን ሲጫወቱ ይታያል፡፡ እንደሚሞቱ ቢያውቁም፣ ቅጽበታቸውን ብቻ መኖር ጀመሩ፤ የሚወዱትንም ሙዚቃ ከልባቸው ተጫወቱ፡፡
እንደ ካምዩ እሳቤ የሰው ልጅ የሚኖርበት ምክንያት ከሌለው philosophical suicide ይፈጽማል፡፡ ይህም ማለት ሕይወት ትርጉም ባይኖራትም ትርጉም እንዳላት አድርጎ ማሰብ ይጀምራል። ለዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ የሚሆኑት ጭፍን አማኞች ናቸው፡፡ በእምነት ውስጥ መመርመር የለም... የምትኖርበት አላማ እንዳለህ እና የምታምንበት ሀይል ለዚህ አላማ እንደፈጠረህ ያለምንም መጠራጠር በጭፍን ትቀበላለህ፡፡ ስለሆነም መኖርህ ዋጋ አልባ ወይም ዘበት እንደሆነ አይሰማህም፡፡
ሌላኛው ደግሞ የምናገኘው ካምዩ absurd hero ይለዋል። ይህ ሰው ሕይወቱ ትርጉም እንደሌላት ያውቃል፤ ለሌሎች ሰዎች ትርጉም የማይሰጥ ነገር ግን ለእርሱ ብቻ ዋጋ ያለው ... ለእርሱ ብቻ የሚሰራ የሕይወት ትርጉምንም ይፈጥራል። ይህ የትርጉም ፈጠራ ሂደትም በራሱ ደስተኛ ያደርገዋል። ለሲሲፈስም ድንጋዩን ወደ ተራራ ማንከባለሉ ለእርሱ ትርጓሜ አለው፡፡ ይህ ለስው ልጆች የከፈለው መስዋእትነት ምልክት ነው. ይህ አማልክቱ ለእርሱ የሰጡት ቅጣት ምንም እንዳልሆነ ማሳያ መንገዱ ነው... ፈገግ ብሎም ድንጋዩን ይገፋል... የእርሱ ፈገግታም አማልክቱን እንደሚያስቆጣቸው ያስባል። እናም ድንጋይ ማንከባለሉ ብቻ ልቡን በደስታ ይሞላዋል።
ካምዩም ሕይወት ትርጉም አልባ እንደሆነች ቢያውቅም እንኳ እንደ ሲሲፈስ ሁን ይልሃል። በዝናብ ውስጥ ደንስ... ትርጉም አልባ በሆነች ዓለም ላይ ለራስህ ብቻ እውነት የሆነ የመኖር ትርጉም ፍጠር፡፡
ምንጭ ፦ ፍልስፍና ከዘርዓያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ
ምንጭ ፦ ፍሉይ አለም
5.2K viewsCeku'aa, edited 10:09