Get Mystery Box with random crypto!

ኢቮሊውሽን - ፩ ( Dec. 16, 2019 የተጻፈ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የ | ምስባከ ጳውሎስ (Paul's Pulpit)

ኢቮሊውሽን - ፩

( Dec. 16, 2019 የተጻፈ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማቱን ሲቀበሉ፣ የኖቤል ኮሚቴው ሊቀ መንበር ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በማውሳት፣ “በዚህ ረገድ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን” በማለት ተናግራ ነበር። ንግግሯ ጮቤ ካስረገጣቸው ሰዎች መካከል ክርስቲያኖችም አሉበት። ይህ ግን በአንዳንድ ወገኖች ላይ የጥያቄና የተቃውሞ ሰበብ ሆኖ ታይቷል። “ዓለም የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት የተቀበለው ከሉሲ በመነሣት ነው፤ ይህ ግን የሰው ልጅ በአዝጋሚ ለውጥ ከዝንጀሮ መሰል እንስሳ ወደ ሰው-ነት እንደ ተቀየሩ ለሚያስቡቱ እንጂ ለክርስቲያኖች የሚመጥን አይደለም። እናስ እንዴት ክርስቲያን በዚህ ይደሰታል?” የሚሉ ሐሳቦች እየተወረወሩ ነበር።

ስለዚህም በክርስቲያናዊ አስተምህሮ እና በአዝጋሚ ለውጥ አስተሳሰብ መካከል ያለው መስተጋብር ምን እንደሚመስል ውስን ሐሳቦችን በዚሁ አጋጣሚ ማንሣቱ ተገቢ ይመስለኛል። (በነገራችን ላይ ብዙዎቻችን ሉሲ ጋ ቆመናል እንጂ፣ የሉሲ ታላቅ የሆነችው አርዲን ያስታወስናት አልመሰለኝም።)

ጥንተ ፍጥረትን በሚመለከት ከሚቀርቡ ክርስቲያናዊ አስተሳሰቦች መካከል የምድርን ወጣትነት የሚያወሳውን ለዛሬ እንመለከታለን፤ ከነስሙም “Young Earth” በመባል ይታወቃል። በዚህ አስተሳሰብ መሠረት የምድር ዕድሜ ከ6 ሺህ እስከ 10 ሺህ ዓመት ቢሆን ነው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረባቸው በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ያሉት 6 ቀናት እያንዳንዳቸው 24 ሰዓት ያላቸው ቀናት ተደርገው ስለሚታሰቡ ነው። ስለዚህ ምድርና ሞላዋ የተፈጠሩት በ6 ቀናት ውስጥ ነው። ከዚያ አዳም ከኖረበት ዕድሜ በመነሣት፣ የሌሎችንም ዕድሜ ደማምረው በሺ የሚቆጠሩ ዓመታት ላይ ይደርሳሉ። በዚህ ጎራ ውስጥ ያሉ ሰዎች አዳም ከውድቀት በፊት የነበረውን ዕድሜም ከግምት የሚከትቱ አይመስለኝም። ስለዚህ ይህን ሐሳብ የሚቀበሉ ሰዎች፣ ሳይንስ የምድርን ዕድሜ (እናም የመላለሙን) በሚሊዮኖችና በቢሊዮኖች ማስላቱን ከቅጥፈት ይቆጥሩታል። የቅሪተ አካላት ግኝትንም በጭራሽ አይቀበሉም።

ፍጥረታት ሲጠኑ ከዕድሜያቸው በላይ የሚመስሉት ከመጀመሪያም "ባለ ትልቅ ዕድሜ" ሆነው ስለ ተፈጠሩ ነው። ለምሳሌ አዳም የተፈጠረው ለአካል መጠን የደረሰ ሰው ሆኖ እንጂ ጨቅላ ሆኖ አይደለም። የዚያን ቀን (ወይም በማግስቱ) ዕድሜው 1 ቀን ብቻ ቢሆንም፣ ሲታይ ግን ጎልማሳ ነው። ሔዋንም በተፈጠረችበት የመጀመሪያ ቀኗ ላይ ለአካለ መጠን የደረሰች ኮረዳ ነበረች። ስለዚህ አዳምና ሔዋንን አግኝቶ የሚመራመር ሰው በምድር ላይ ከኖሩበት ዕድሜያቸው በላይ ነው የሚገምታቸው።

ልክ እንደዚሁ እግዚአብሔር ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ዐለቱን፣ ወንዙን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትን ሲፈጥር ሚልዮን ምናምን ዓመታት የሞላቸው አድርጎ ፈጥሯቸው ቢሆንስ? ልክ አዳምና ሔዋንን ዐዋቂ ሰዎች (adults) አድርጎ እንደ ፈጠራቸው ማለት ነው። በዚህም ላይ የጥፋት ውሃ መከሰት አንዳንድ መልክዐ ምድሮች ከትክክለኛው ዕድሜያቸው በላይ የተጋነነ ዕድሜ ያላቸው እንዲመስል ማድረጉን ለዚህ በማስረጃነት የሚጠቅሱ ሰዎችም አሉ። ለእነዚህ ሰዎች አዝጋሚ ለውጥ ብሎ ነገር አንዳችም እውነትነት ስለ ሌለው፣ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ከሺዎች ዓመታት በፊት ሲፈጠሩ የነበራቸው መልክ ይዘው ቆይተዋል እንጂ ከቶ አልተለወጡም። ስለዚህ ምድር ከተፈጠረች ገና 6 ሺ ዓመታት ገደማ ነው።

በአገራችን በርካታ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ምድባቸው እዚህኛው ጎራ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም የምድርን ዕድሜ ወደ 10 ሺውም አያደርሱትም። በየስብከቱም የምንሰማው ይህንኑ ነው፤ ምድር ከተፈጠረች 6 ሺህ ዓመቷ እንደ ሆነ ስለ ደቀ መዝሙርነት ባሳተመው መጽሐፉ ላይ የጠቀሰ መጋቢም ዐውቃለሁ። ኦርቶዶክሳውያኑም ቢሆን፣ ከአዳም እስከ ክርስቶስ 5 ሺህ ዓመት፣ ከክርስቶስ በኋላም 2 ሺህ ዓመት ስለ መሆኑ በይፋ ያስተምራሉ። ስለ 8ኛው ሺህ የሚያቀርቡት ንግርትም ከዚህ ጋር አንዳች ትይይዝ አያጣውም።

ለማንኛውም፣ እዚህ ሰፈር የለሁበትም!

እያየን እንጨምራለን።

https://t.me/PaulosFekadu