Get Mystery Box with random crypto!

'#እባክህን_ከእሳቱ_ላይ_አትውረድ' አንድ ወንድም አባ ጴሜንን 'ምከረኝ' ብሎ ጠየቀው። አባ | ጳልቃን የማኀደረ ጻድቃን ሰ/ት/ቤት የቴሌግራም ገፅ (ቻናል)

"#እባክህን_ከእሳቱ_ላይ_አትውረድ"

አንድ ወንድም አባ ጴሜንን "ምከረኝ" ብሎ ጠየቀው። አባ ጴሜንም "ድስት በእሳት ላይ እያለ ምንም አይነት ተባይ ሊቀርበውና ሊያበላሸው አይችልም። ከእሳት ወጥቶ ሲቀዘቅዝ ግን ነፍሳት ሁሉ ለመግባትና ለማበላሸት ይቻላቸዋል። ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ተግባር ካልራቀ ጠላት የድቀት ምክንያት አያገኝበትም" አለው።

ወዳጄ ሆይ ሕይወት ቀዝቅዛብሃለችን? ከእሳቱ ወደ መሬት ወርደህ በርደሃልን? የሕያውነትህ ሙቀት እሳት በማጣት ተንዘፍዝፏልን? ድስት የተባለ ሰውነትህ ክረምት የሚያህል ጉድን ተሸክሟልን? ዙሪያ ገባህ ፀሐይ እንደማትወጣበት ምእራብ ጨለማን የሚጠራ ሆኗልን? ማንነትህ እሳት እንዳጣ ምግብ ጥቃቅን ነፍሳት በተባሉ ኃጢአቶች (ቁጣ፣ ቸልተኛነት፣ ስስት፣ አልታዘዝ ባይነት፣ ጭንቀት፣ ሁሉን የመናቅ ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ...) ተወርሮ፣ መዓዛ ቅድስና ተለይቶት እጅ እጅ ብሏልን? ሞቅ የሚያደርገው አጥቶ በዓለማዊነት ሻግቷልን? የተባዮች መጫወቻ፣ የተውሳኮች መቀለጃ ሆኗልን? እንግዲያውስ በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ወዳጄ ሆይ ሃይማኖት በተባለችና ከሰማይ በወረደች ልዩ እሳት (ሉቃ.12፥49) ላይ ተቀምጠህ የድስትነትህን ሙቀት መልስ፡፡ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር (1ቆሮ.13፥13) በተባሉ ሦስት ጉልቻዎች ላይ በምቾት ተጥደህ የሕይወትህን የኃጢአት ብርድ አስወግድ፡፡ ንስሐ በተባለች ነበልባል ውበትነት የክረምትህን ጽልመት በምስራቃዊ በጋነት ድል ንሳ፡፡ በሥጋ ወደሙ ፍምነት ድስት የተባለ ሰውነትህን በከዊነ እሳትነት ቀድስ፡፡ እባክህን በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ሃይማኖት የተባለ እሳትን ተባይ አይቀርበውም፡፡ እምነት ተስፋና ፍቅር የተሰኙ ጉልቻዎችን ተውሳኮች ሽቅብ አይወጡአቸውም፡፡ የነበልባለ ንስሐን ብርሃንና ሙቀት ነፍሳተ ጽልመት መቋቋም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በእሳቱ ላይ እስካለህ ድረስ (በመንፈሳዊ ተግባራት እስከጠነከርክ ድረስ) አንተ ሁሌም ከተባይና ከነፍሳት ብልሽት (ከአጋንንት) የራቅክ ነህ፡፡

ወዳጄ እባክህን ከእሳቱ ላይ አትውረድ፡፡ እሳቱ በደንብ ይነድ ዘንድ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት የተባሉ እንጨቶችንና ምጽዋት የተባለ ጋዝን መጨመርህን እንዳትዘነጋ፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ድስትነት ሁሌም የሞቀ ይሆናል፡፡ እጅ እጅ ከማለት፣ ከመሻገትና የተባይ መጫወቻ ከመሆን ትድናለህ፡፡

ወዳጄ ሆይ እባክህን ከእሳቱ ላይ አይትውረድ፡፡

በኃጢአት "እጅ እጅ '' ከማለትና በበደል ከመሻገት እግዚአብሔር ይሠውረን! አሜን!

(ሕሊና በለጠ ዘኆኅተብርሃን)