Get Mystery Box with random crypto!

ለአመታት ተደብቆ የሚያድገው 'ደስሞይድ' እጢ ————————————————— ዶ/ር ሠዒድ መሐመድ (የ | ♒Orthopedic Surgery in Ethiopia ♒

ለአመታት ተደብቆ የሚያድገው "ደስሞይድ" እጢ
—————————————————
ዶ/ር ሠዒድ መሐመድ (የአጥንት ስፔሻሊስት)
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የዛሬው ባለታሪክ የአርባ ዘጠኝ ዓመት ጎልማሳ ሲሆን እኔ ዘንድ ለህክምና የመጣው  ላለፉት ጥቂት ወራት እግሩ አካባቢ የመወጠር ስሜት እየተሰማው ስለነበረ "ለማንኛውም ልታየው" በማለት ብቻ ነበር።

ምርመራዎች ሲደረጉ ግን እግሩ ውስጥ ትልቅ መጠን ያለው ዕጢ እንዳለ ስለተረዳን የእጢውን ባህሪ እና ምንነት ከገለፅኩ በኋላ አሁን ያለበት ሁኔታ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልግበት ደረጃ እንደሆነ ለታካሚው አስረዳሁት። ሆኖም ታካሚው ለመራመድም ሆነ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለመከወን ምንም ስላልተቸገረ እና እኔ ዘንድ የመጣውም ለወራት ያህል ዛሬ ነገ እሄዳለሁ እያለ ቆይቶ ሰሞኑን ስለተመቸው ብቻ እንጂ ለቀዶ ህክምና የሚያበቃ ችግር ይኖርብኛል ብሎ በፍፁም ስላልገመተ የምርመራ ውጤቱን ለመቀበል ተቸገረ።

በስተመጨረሻ ግን ውጤቱ ትክክል እንደሆነ፣ ምንም እንኳን ከውጪ የሚታይ ግልፅ እባጭ ወይም የከፋ የህመም ስሜት ባይኖረውም፣ በምርመራ ውጤቱ መሠረት እስከ 17 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ትልቅ ዕጢ ጡንቻው ውስጥ መኖሩ እንደተረጋገጠ አስረድቼው ፣ ሁኔታውን ስለተገነዘበ ለቀዶ ህክምና ዝግጁ ሆነ።  በዕርግጥም ዕጢው መጠኑ ከፍ ያለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለእግር በህይወት መቆየት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ዋና ዋና የደም ስሮች እና ነርቮችን ተጭኖ የነበረ በመሆኑ ቀዶ ህክምናውን ስናደርግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አስፈልጎን የነበረ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ምስሉ ላይ የሚታየው ዕጢ ያለምንም ተከታይ ጉዳት ሊወጣለት ችሏል።

ደስሞይድ ዕጢ ምንድነው?
————————————
ደስሞይድ ዕጢ ከአንድ ሚሊየን ሠዎች ውስጥ ከሁለት እስከ አራት ሰዎችን የሚያጠቃ የስስ ጡንቻ ዕጢ ሲሆን፣ ልክ እንደዛሬው ባለታሪካችን መኖሩ ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ጥልቅ አካል ውስጥ ሊቆይ ይችላል።  ይህ ዕጢ የካንሰርነት ባህሪ የሌለው እና ወደ ካንሰር የመቀየር ዕድሉም ጠባብ እንደሆነ በበርካታ ጥናቶች የተስተዋለ ቢሆንም፣ እያደገ ሲሄድ ግን በዙሪያው ያሉ የነርቭ እና የደም ስሮችን በመጉዳት በሂደት ከፍተኛ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

በመሆኑም ከሐኪም ጋር እየመከሩ የዕድገቱን ሁኔታ በመከታተል እንደ ሁኔታው ቀድሞ የተሻለውን የህክምና አማራጭ መወሰን እና ሊከተል የሚችልን ችግር ቀድሞ መቅረፍ ወሳኝ ነው።
—————————————————
Take home message: ሠውነት ላይ የሚሠማን የህመም መጠን የችግሩን መጠን ላያሳይ ይችላል!
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ለዚህን መሠል መረጃዎች በነዚህ አድራሻዎች ይከተሉን:

YouTube: " Doctor Seid"

የቴሌግራም ቻናል: https://t.me/patientstories

የፌስቡክ ገፅ: የአጥንት ህክምና/Orthopedic Surgery (https://www.facebook.com/EthioOrthopedics/)

ስልክ: 6194