Get Mystery Box with random crypto!

ማስታወሻ ለኢትዮጲያ ህክምና ማህበር (EMA) ——————————————————— ዶ/ር ሠኢድ መሐመድ | ♒Orthopedic Surgery in Ethiopia ♒

ማስታወሻ ለኢትዮጲያ ህክምና ማህበር (EMA)
———————————————————
ዶ/ር ሠኢድ መሐመድ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ሠሞኑን ከአንድ የኩላሊት ህክምና ስፔሻሊስት የስራ ባልደረባዬ ጋር ሁለታችንም ስለምናውቃቸው ስለአንድ ታካሚ ጉዳይ ስንወያይ ነበር። ታካሚዋ አስቸኳይ የኩላሊት እጥበት ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው በተለያዩ የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪሞች ቢነገራቸውም ውሳኔውን መቀበል (ሐኪሞቹን ማመን) አልፈለጉም። ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ሌሎች ስፔሻሊስቶችን ሲያማክሩ፣ የሁሉም ውሳኔ ተመሳሳይ ቢሆንም ውሳኔውን መቀበል ተቸግረው ከሐገር ውጪ ሄደው የውጭ ሃኪሞችን ማማከር በመፈለጋቸው እስከአሁን እጥበት እንዳልጀመሩ አጫወተኝ። የጤናቸው ሁኔታም ቀናት በጨመሩ ቁጥር እየከፋ በአሁኑ ሰአት የውጪው ፕሮሰስ እስኪሳካ ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጧል።

ይህንን መሠል ገጠመኞች በየስፔሻሊቲ ዘርፉ የሚያጋጥሙ ናቸው። በዚህ በሐኪም እና ታካሚ ያለመተማመን ሂደት ውስጥ ግን ዋነኛ ተጎጂው ልክ ከላይ እንደጠቀስኩት ምሳሌ ታካሚው (ህብረተሰቡ) ነው። ይህ ችግር ከየት መጣ? ካልን ግን የችግሩ መንስኤ ከስንት አንድ ጊዜ የሚከሰቱ እና በየትኛውም ዓለም የሚያጋጥሙ የህክምና ስህተቶችን ከሚገባው በላይ በማጋነን እና የሆነውንም ያልሆነውንም በመጨማመር፣ ከዚያም አልፎ የኢትዮጲያዊያን የጤና ባለሙያዎች ብቻ ችግር አስመስለው የሚያቀርቡ ሚዲያዎቻችን ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው።

በእኔ እይታ ሁለተኛው ተጠያቂ ደግሞ በጤና ባለሙያዎች ላይ ያልተገባ ውሸት ሲነዛ እና የበሬ ወለደ አሉባልታ ሲወራ ምንም እንደማይመለከታቸው እጃቸውን አጣጥፈው የሚመለከቱት የህክምና ማህበራት ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ከዋናው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር (EMA) ጀምሮ በተለያዩ ስፔሻሊቲዎች እና የሙያ ዘርፎች ተደራጅተው ህጋዊ ሠውነት ያላቸው ማህበራት (societies) ቢኖሩም የሁሉም ሚና አመታዊ ስብሰባ ከማዘጋጀት እና ከአጫጭር ስልጠናዎች የዘለለ አይደለም። አለመታደል ሆኖ ይህ ባህል ከድሮውም በጤና ማህበራት የተለመደ ሆነ እንጂ፣ እንደ ሙያ ማህበርነታቸው፣ ሙያቸው ላይ ወይም አባላቶቻቸው ላይ ከመንግስትም ይሁን ከግለሰብ ወይም ከሚዲያ ተቋማት የሚደርሱ የህግ ጥሰቶችን ተከታትለው ክስ በመመስረት በመዋጮ የሚያኖሯቸውን አባላቶቻቸውን እና ሙያቸውን ማስከበር መሠረታዊ ተግባራቸው ሊሆን ይገባ ነበር።

ለአብነት ያህል ሰሞኑን አርቲስት ሃና ዩሐንስ አንዲት በካንሰር ህመም ምክንያት እግሯ በቀዶ ህክምና እንዲወገድ የተደረገላትን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ታካሚ ጋብዛ ባደረገችው ቃለ ምልልስ ሁለቱም እየተቀባበሉ የሚያወሩት የጤና ባለሙያዎቹ ምን ያህል ሥነምግባር የጎደላቸው እንደሆኑ፣ ምን ያህል ዕውቀት እንደሌላቸው፣ ወዘተ… ነው።

ይህንን መነሻቸውን ለማጠናከርም በተለይም ታካሚዋ በቀዶ ህክምና ወቅት ደረሰብኝ ያለችውን የነርቭ ጉዳት አርቲስት ሃና ሙሉ ለሙሉ በመቀየር እና ተመልካችን ለመሳብ ምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት "በስህተት እግሬን ቆረጡት" በሚል ነጭ ውሸት ቀይራ አቅርባዋለች። ርዕሱ ገርሞኝ ቪዲዮውን ስመለከተው ግን ሃና ልጅቷን ያከሟት ሐኪሞች (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል) "በስህተት እግሯን ቆረጡ" የሚል መልዕክት እንዲኖረው አድርጋ ያቀረበችው ክስተት በፍፁም ያልተከሰተ ከመሆኑም በላይ፣ ልጅቷ የምትገልፀው ከነአካቴው እግር የማስወገዱ ቀዶ ህክምና የተካሄደው ደቡብ አፍሪካ እንደሆነ ፣ ያከሟት ሃኪሞችም ያንን ያደረጉት በስህተት ሳይሆን በካንሰር ምክንያት በመሆኑ በመቁረጣቸው ህይወቷን እንዳተረፉ ነው። በበኩሌ በስህተት እግር መቁረጥን የሚያክል ዕምነት የሚያጠፋ ከባድ ዜና እንደቀልድ ዋሽቶ መለጠፍ ያለተጠያቂነት ማለፍ አለበት ብዬ አላምንም።

አርቲስቷ ይሄንን ትኩረት የሚስብ የቪዲዮ አርዕስት ስትመርጥ ያሳሰባት "ስንት ሰው የሄንን ቪዲዮ ተመልክቶ ምን ያህል ገንዘብ አገኝ ይሆን?" የሚለው ነው እንጂ በዚህ ውሸቴ ምክንያት በሚበላሸው የታካሚ እና የሐኪም ግንኙነት የስንት ሰው ህይወት ይበላሽ ይሆን? የሚለው አይደለም። ይሄንን ድፍረት ያገኘችውም ሁሉም የፈለገውን ያህል ዋሽቶ ሲጠቀም እንጂ ተጠያቂ ሲሆን ስላላየች ነው። ታዲያ ለምሳሌ እንኳን በዚህ ቪዲዮ ላይ ስማቸው እንዲጠለሽ የተደረጉትን ባለሙያዎች በአባልነት ያቀፉ ተቋማት (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፣ የኢትዮጵያ የአጥንት ህክምና ማህበር፣ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር) በዚህ ጉዳይ ዝምታን መምረጥ አለባቸው?

በተለይም የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር (EMA) እንደዚህ አይነት በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ዕውቅና ተጠቅመው ሙያውን የሚያጠለሹ አርቲስቶችን እና ጋዜጠኞችን ወደህግ በማቅረብ አንድም ለሚዲያ ባላቸው ቅርበት ምክኒያት የባለሙያውን ስም ዳግም እንዳሻቸው እንዳያጎድፉ ማድረግ፣ በሌላ በኩልም እንደነዚህ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች ወደህግ ቢቀርቡ ዜናው በቀላሉ ስለሚዳረስ ሁሉም ዜናው የደረሰው አካል የጤና ባለሙያዎችን በሐሰት ከመዝለፉ በፊት ቆም ብሎ እንዲያስብ መማሪያ ይሆናልና ጉዳዩ በዝምታ እንዳይታለፍ እጠይቃለሁ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
Follow us on:
YouTube: " Doctor Seid"
የቴሌግራም ቻናል: https://t.me/patientstories
የፌስቡክ ገፅ: የአጥንት ህክምና/Orthopedic Surgery (https://www.facebook.com/EthioOrthopedics/)