Get Mystery Box with random crypto!

​​​​ #የቀጠለ የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ “በ | ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ አገልግሎት

​​​​ #የቀጠለ

የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ “በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል..” (ዳን.12፡1) በማለት ተናግሮለታል ፡፡

ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው። ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡

እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መሾሙ እጅግ ትሑትና ስለመንጎቹ ነፍሱን እንኳ አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለሚወዳቸው ነበር፡፡ (ዘኁል.12፡3፤ዘጸአ.32፡32)በሕዝቡም ላይ እርሱን መሾሙ እንዲሠለጥንባቸው ወይም እንዲገዛቸው ሳይሆን በትምህርቱና በጸሎቱ እነርሱን እንዲያግዛቸው ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለሙሴ ሲመሰክር “እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው”አለ፡፡ (የሐዋ.7፡35)

እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እጅግ ትሑትና ለሠራዊቱ ተቆርቋሪ የሆነ መልአክ በመሆኑ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ተሾመ፡፡ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙ ልክ እንደ ሙሴ በእነርሱ ላይ ሊሠለጥንባቸው ወይም ሊገዛቸው ሳይሆን መላእክትን ሊመራ ፣ እኛን ደግሞ ከሰይጣን ጥቃት ሊጠብቀንና በጸሎቱ ሊራዳን ነው (ይሁዳ.12) ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት እኛን እንደሚጠብቁና እንደሚራዱ እንዲሁም ስለእኛ በፊቱ አንደሚቆሙ ሲያስተምረን “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁል ጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ” (ማቴ.18፡10) ብሎናል፡፡

እኛን ይጠብቁ ዘንድ የተሰጡን ቅዱሳን መላእክት ስለእኛ እንዲህ የሚቆረቆሩና ስለመዳናችን የሚተጉ ከሆነ በቅድስናው ልቆ የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ሚካኤል እንዴት ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ አይቆም? (ሉቃ.13፡6-9) እንዴትስ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል አይረዳን? (መዝ.33፡7) እርሱ “ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው” መባሉም እኛን በጸሎቱና በተራዳኢነቱ የጽድቅ ሕይወታችንን በሚገባ እንድናከናውን እንደሚራዳን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው፡፡

የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ለዘለዓለሙ ይደርብን አሜን፡፡

#ምንጭ፦ የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መልአከ ሠላም ሰንበት ትምህርት ቤት ገጽ

@ortodoxtewadochannal
@ortodoxtewadochannal
@ortodoxtewadochannal