Get Mystery Box with random crypto!

​​በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማስመልከት ከኢትዮጵያ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማስመልከት ከኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ ፤


"ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።" 1ኛ ጴጥርስ 4፥12:13

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ  አሜን       

በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በጥብቅ እናወግዛለን፤ የጸጥታ ተቋማትም ጥቃቱን እንዲከላለሉ እንጠይቃለን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአርሲ ዞን በሹርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተክርስቲያናት ላይ በተለያዩ ጊዜያት 36 ኦርቶዶክሳዊያን በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ሀገረ ስብከቱ ባደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል።

በዚሁ ጥቃት በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች 28 ኦርቶዶክሳዊያን ከየቤታቸው ተለቅመው የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 7ቱ ሴቶችና 21ዱ ወንዶች መሆናቸው ታውቋል። በዚህ ጥቃትም እድሜያቸው ከሰባ ዓመት አዛውንት እስከ ሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ ሕጻናት ይገኙበታል። በዛሬው ዕለት ደግሞ በዲገሉ ማርያም ቤተ ክርስቲያን 5 ኦርቶዶክሳዊያን ከመገደላቸው በተጨማሪ የሦስት ኦርቶዶክሳውያን ቤት ደግሞ ተቃጥሏል። 

ከዚህ ቀደም በሮቤ አንዲቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም ቤተክርስቲያን በዓለ ማርያምን አክብረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ ሦስት ኦርቶዶክሳዊያን ጨለማን ተገን ባደረጉ ነፍሰ ገዳዮች መገደላቸው ይታወሳል።

የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በተደጋጋሚና ሆን ተብሎ በሚፈጸመው የኦርቶዶክሳዊያን ጥቃት ዙሪያ በጋራ እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን በዚህ ዐይነት የጥቃት ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ አካላት ላይ በመንግሥት በኩል የማያዳግም ርምጃ እንደተወሰደባቸው ሀገረ ስብከቱ  በላከው ሪፖርት አረጋግጠዋል።

ይህ ዐይነት ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በምእመናን ላይ መድረሱ አግባብነት የሌለውና እምነትን በነጻነት የማራመድ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ በመሆኑ መሰል  ሕገ ወጥ ጥቃትን ለመከላከልና  ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መብቶቻቸውን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ማስከበር እንዲችሉ  ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱን በማውገዝ ችግሩ ከመሠረቱ እንዲፈታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ ሲገባው በዝምታ በማለፉ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቷታል።

ይህ ዐይነቱ ኦርቶዶክሳዊያን ላይ ያነጣጠረ ግድያ እንዲቆምና የወንጀሉ ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ በሀገረ ስብከቱ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም በድርጊቱ እጅጉን ማዘኑን እየገለጸ ጉዳዩን  ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር  በመሆን የሚከታተለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

በሌሎች ስፍራዎች የሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ጥቃቶችን በእንጭጩ ለመቅጨትና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት ይቻል ዘንድ አህጉረ ስብከት ችግሮች በሚያጋጥሙ ወቅት ሪፖርት እንዲልኩ ቀደም ሲል በደብዳቤ በተላከላቸው የስልክና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት በፍጥነት በማሳወቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እያሳሰብንና ለሞቱት ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ሁሉ ልዑል እግዚአብሔር መንግሥተ ሰማያትን እንዲያወርስልን በመጸለይ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት የሚደርሱ ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙና መሰል ጥቃት እንዳይፈጸም ለኦርቶዶክሳዊያን ወገኖቻችን ከለላ እንዲሰጡልን እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት

ምንጭ: የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ