Get Mystery Box with random crypto!

​​✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን፡፡ ✞✞✞ ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን፡፡ ✞✞✞

ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ

እንደ አባቶቻችን ትርጉም 'ፊልዾስ' ማለት መፍቀሬ አኃው ወንድሞችን የሚወድ' ማለት ሲሆን ከ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ነው:: (ማቴ. 10:3) በዚህ ስም የሚጠራ ሐዋርያ ከ72ቱ አርድእት ውስጥ ነበር:: እርሱም ጃንደረባውን ባኮስን ያጠመቀው ነው።

አንዳንዴ የ2ቱ ታሪክ ሲቀላቀል እንሰማለን:: ለሁሉም ይህኛው ቅዱስ ፊልዾስ ቁጥሩ ከ12ቱ ሐዋርያት ሆኖ ምሑራነ ኦሪት ከሚባሉትም አንዱ ነበር:: በወቅቱ ገማልያል የሚሉት ክቡርና ምሑረ ኦሪት በርካታ ምሑራነ ኦሪትን አፍርቶ ነበር::

እንደ ምሳሌም ቅዱሳኑን "ዻውሎስን: ኒቆዲሞስን: ናትናኤልን: እስጢፋኖስንና የዛሬውን ሐዋርያ ቅዱስ ፊልዾስን" መጥቀስ እንችላለን:: ቅዱስ ፊልዾስ ነገዱ ከእሥራኤል ሲሆን ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ ነው:: ኦሪትን ተምሮ በመንገድ ዳር ቁጭ ብሎ 'መሲሕ ቀረ' እያለ ሲተክዝ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ደረሰ::

ትክ ብሎ አይቶት "ተከተለኝ" አለው:: (ዮሐ. 1:44) ቅዱስ ፊልዾስም ያለ ማመንታት: ሁሉን ትቶ በመንኖ ጥሪት ተከተለው:: በዚህ ዓይነት ጥሪ መድኃኒታችን ቅዱስ ማቴዎስንም ጠርቶታል:: (ማቴ. 9:9) ቅዱስ ፊልዾስ ጌታን ከተከተለ በሁዋላ ሥራ አልፈታም። ወዲያውኑ ሒዶ ለናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) ሰበከለት እንጂ።

"ሙሴ በኦሪት: ነቢያትም የተነበዩለትን መሲሕን አግኝቸዋለሁ" አለው:: ይሕ አነጋገሩም ምሑረ ኦሪት እንደ ነበር በእርግጥ ያሳያል:: (ዮሐ. 1:46) ቅዱስ ናትናኤልም ምሑር ነውና "ከናዝሬት ደግ እንዴት ይወጣል?" ቢለው ቅዱስ ፊልዾስም መልሶ "ነዐ ትርአይ-ታይ ዘንድ ና" አለው::

ናትናኤልም ሒዶ በጌታ አመነ:: ቅዱስ ፊልዾስ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን በዮሐንስ ወንጌል ተደጋግሞ ስሙ ተጠቅሷል:: በተለይ ደግሞ ጌታ የ5 ገበያ ሕዝብን አበርክቶ ሲመግብ አስቀድሞ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር:: እርሱ ግን "ጌታ ሆይ! የ200 ዲናር እንጀራ ብንገዛም አንዘልቀውም" ብሎ ነበር::

በሁዋላ ግን የጌታን ድንቅ ተአምር ተመለከተ:: (ዮሐ. 6:5) በተለይ ደግሞ በሐዋርያት አበው መካከል ለጌታ እንደ እንደራሴ ሆኖ ያገለግል እንደ ነበርም ተጠቅሷል:: ሰዎች ጌታን ማግኘት ሲፈልጉ እሱና እንድርያስን ያናግሩ ነበር:: (ዮሐ. 12:20) አንድ ጊዜ ግን እስካሁን ሊቃውንትን የምታስደምም ጥያቄ ጠይቆ ነበር::

አጠያየቁ ደግሞ ፍጹም የዋሕ እንደ ሆነ ያሳያል:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ባሕርይ አባቱ አብ እየነገራቸው ሳለ ቅዱስ ፊልዾስ ከመካከል ተነስቶ "እግዚኦ አርእነሁ ለአብ ወየአክለነ": ልክ ወልድን በዐይኑ እንዳየ ሁሉ አብን ሊያይ ቸኩሎ "አቤቱ ስለ አብ የሰማነው ይበቃልና አሳየን" ብሎታል:: (ዮሐ. 14:8)

ጌታችን ግን "ዘርእየ ኪያየ ርዕዮ ለአብ-እኔን ያየ አብን አይቷል" (ዮሐ.14:9) ብሎ ምሥጢረ ባሕርዩን: አንድነቱን ሦስትነቱን አስረድቶታል:: ቅዱስ ፊልዾስም ጌታን እስከ ሕማሙ አገልግሎ: ቅድስት ትንሳኤውን አይቶ: ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ: ቅዱስ መንፈሱን ከ72 ልሳን ጋር ነስቶ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ሲካፈሉ ለእርሱ አፍራቅያ (አፍሪካ) ደርሳዋለች:: ስለዚህም በምድረ አፍሪካ ወንጌልን ከሰበኩ ሐዋርያት አንዱ ነው:: በአፍራቅያና በቀድሞው የኃምስቱ አሕጉር ግዛት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጐ ብዙዎችን ወደ መንጋው (ወደ ክርስትና በረት) ቀላቀለ::

ለበርካታ ዓመታትም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ: ብርሃነ ክርስቶስን ሲያበራ: ነፍሳትንም ሲማርክ ቆየ:: ገድለ ሐዋርያት እንደሚለው የቅዱስ ፊልዾስ ፍጻሜው በሰማዕትነት እንደ ሆነ ቢታወቅም የትኛው ሃገር ውስጥ እንደ ሆነ መለየት አልተቻለም::

ዜናው ግን እንዲህ ነው:- በአንዲት ሃገር ውስጥ ገብቶ ሰበከ:: ብዙዎችንም አሳመነ:: ያላመኑት ግን ይዘው አሰቃዩት: ገረፉት:: "በክርስቶስ እመኑ እባካችሁ!" እያለ እየለመናቸው ዘቅዝቀው ሰቅለው ገደሉት::

ከዚያም በእሳት እናቃጥላለን ሲሉ ቅዱስ መልአክ ከእጃቸው ነጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው:: በዚህ የደነገጡት ገዳዮቹ ለ3 ቀናት ጾሙ: ተማለሉ:: በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሥጋ ተመልሶላቸው: ገንዘው ቀብረውት በክርስቶስ አምነዋል::

አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ ሲል ቸርነቱን: ምሕረቱን ይላክልን። ከበረከታቸውም ይክፈለን።

ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሼር አድርጉ
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur