Get Mystery Box with random crypto!

​​እንኳን ለዓለም ሁሉ መምሕር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኳን ለዓለም ሁሉ መምሕር ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው?

ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

ከዚህች እለት በሁዋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

ከዚህ በሁዋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኩዋን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል::

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::

አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ:: (ግብዣ አዘጋጀ) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ 12ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ::

ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ" አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::

በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው::

"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ - የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም' ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::

"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኩዋ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::

'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው?' እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በሁዋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::

አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች::

ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል::

ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን: በዚህ ቀን ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጉዋል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኩዋል::

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:-
- ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
- አፈ በረከት
- አፈ መዐር (ማር)
- አፈ ሶከር (ስኩዋር)
- አፈ አፈው (ሽቱ)
- ልሳነ ወርቅ
- የዓለም ሁሉ መምሕር
- ርዕሰ ሊቃውንት
- ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
- ሐዲስ ዳንኤል
- ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
- መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
- ጥዑመ ቃል

አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ረድኤት በረከት አይለየን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሼር አድርጉ
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur