Get Mystery Box with random crypto!

​​እንኩዋን 'ለቅድስት ወብጽዕት ሐና' እመ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኩዋን "ለቅድስት ወብጽዕት ሐና" እመ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ 

 ብጽዕት ሐና

"ሐና" ማለት በእብራይስጥኛው "የእግዚአብሔር ስጦታ" እንደ ማለት ነው:: "ሐና: ዮሐና: ሐናንያ" የሚሉ የዕብራይስጥ ስሞች ትርጉማቸው ተወራራሽ ነው:: የዚህችን ቅድስት እናት ክብሯን መናገር የሚችል የለም:: እርሷ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ወልድ በሥጋ አያቱ ተብላለችና::

አንድም ለሰማይና ለምድር ንግስት ለድንግል ማርያም ወላጅ እናቷ ናትና:: ከዓለም ሴቶች ሁሉ የቅድስት ሐና ማሕጸን እንደ ምን ይከብር! በፍጥረት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥንተ አብሶ የአዳም በደል መተላለፍ የቀረው በማሕጸነ ሐና ውስጥ ነውና::

ይስሐቅን የተሸከመ የሣራ ማሕጸን ቡሩክ ከተባለ የቅድስት ሐናማ እንደምን አይባል! ከፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን እንደ መረጠ ሁሉ ቅድስት ሐናንም ለአያትነት መርጧታል::

ለመሆኑ ቅድስት ሐና ማን ናት? ለዚህ ክብርስ ያበቃት ምሥጢረ ቅድስናዋ ምንድን ነው?

ቅድስት ሐና ትውልዷ: ነገዷ ከላይ ከቅዱስ አብርሃም: ከታች ደግሞ ከነገደ ካህናት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :- አብርሃም ይስሐቅን: ይስሐቅ ያዕቆብን: ያያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና ፲፩ ወንድሞቹን ይወልዳል:: ሌዊ ቀዓትን: ቀዓት እንበረምን: እንበረም አሮን ካህኑን ይወልዳሉ::

ቅዱስ አሮን አልዓዛርን: አልዓዛር ፊንሐስን እያለ ትውልዱ እስከ ቴክታና በጥሪቃ ይወርዳል:: ቴክታና በጥሪቃም ልጅ በማጣት ኖረው: የእንቦሳዎች: የፀሐይና: የጨረቃን ምሥጢር ተመልክተው ሄኤሜንን ይወልዳሉ::

ሄኤሜን ዴርዴን: ዴርዴ ቶናሕን: ቶናሕ ሲካርን: ሲካርም ሔርሜላን ይወልዳሉ::
ሔርሜላም ከክርስቶስ ልደት ፺  ዓመታት በፊት ማጣት የሚባል ደግ ሰው ከካህናት ወገን አግብታ በስርዓተ ኦሪት ትኖር ነበር:: እግዚአብሔር ለዚህች ደግ ሴት የተባረኩ ፫ ሴቶች ልጆችን ሰጣት::

የመጀመሪያዋን "ማርያም" አለቻት:: ይህቺውም የአረጋዊው ዮሴፍ ሚስትና የቅድስት ሰሎሜ ቡርክት እናት ናት:: ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አለቻት:: እርሷም ቅድስት ኤልሳቤጥን የመጥምቁን እናት ወልዳለች::

በመጨረሻ የወለዷትን ግን "ሐና" አሏት:: ይህቺውም የፈጣሪ የሥጋ አያቱ: የድንግል ማርያምም እናቷ ትሆን ዘንድ የተመረጠችውና ስም አጠራሯ የከበረው: ዛሬ የምናከብራት እናት ናት::

መጽሐፈ ስንክሳርን ስመለከት እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አየሁ:: "ለዛቲ ቅድስት ኢያዕመርነ ገድላቲሃ ዘትገብሮን በኅቡዕ ከመ ንዝክሮን" ይላል:: ትርጉሙም "የዚህቺን ቅድስት ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳንዘረዝር አላወቅነውም" እንደ ማለት ነው::

የሚገርመው አበው እንዲህ ያሉት ክብሯን መግለጹን አልጠግብ ብለው ነው:: እኛም በመጠናችን የብጽዕት ሐናን ሕይወት በአጭሩ ቀጥለን እንመልከት::

ብጽዕት ሐና ወላጆቿ ከካህናት ወገን በመሆናቸው ልጆቻቸውን በጥንቃቄ: በሥርዓተ ኦሪት እንዳሳደጉ ይታመናል:: ቅድስት ሐናንም ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ድረስ በሕጉ: በሥርዓቱ አሳድገዋታል::

በወቅቱ በፈቃደ እግዚአብሔር ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ የሚሆን አንድ ደግ ሰው አጩላት:: ይህ ሰው "ኢያቄም" ይባላል:: አንዳንዴም "ሳዶቅ" ወይም "ዮናኪር" እየተባለ ይጠራል:: ቅዱስ ኢያቄም ማለት ክፉ ከአንደበቱ የማይወጣው: ምጽዋትን የሚወድ: አምላከ እሥራኤልን በንጹሕ ልቡ የሚያመልክ ሰው ነበረ::

እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ፪ቱ ከተጋቡ በሁዋላ ቶሎ መውለድ አልቻሉም:: ይሕ ደግሞ የወቅቱ ከባድ ፈተና ነው:: በዘመድ የከበሩ: በጠባያቸው የተመሰገኑ: መልካምንም የሚሠሩ ሰዎች ልጅ ስለሌላቸው ብቻ "ኅጡአነ በረከት" እየተባሉ ከቤተ እግዚአብሔር ይገፉ: በአደባባይም ይነቀፉ ነበር::

ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ልጅ አለመውለድ እንደ ኃጢአተኛ ያስቆጥር ነበር:: ደግነቱ የወቅቱ ሊቀ ካህናት ቅዱስ ዘካርያስ እንደ እነሱ ልጅ ያጣ በመሆኑ አብረው ይጽናኑ ነበር::

የሆነው ሆኖ እኒህ ቡሩካን ሰዎች አምላከ እሥራኤልን ከመለመንና ከማመስገን በቀር ሌላ ትርፍ አልተገኘባቸውም:: ምንም የሞላቸውና የደላቸው ባይሆኑም ደሃን ሳያጐርሱ አይበሉም ነበር::

ቅድስት ሐናን ግን "ቢወልዷት እንጂ አትወልድ: ድንጋይ: በቅሎ" እያሉ ጐረቤቶቿ ይሳለቁባት ነበር:: ከማልቀስ በቀር ደግሞ መልስ አልነበራትም::

አንድ ቀን ግን ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክታ "ፈጣሪ ሆይ! የእንስሳትን ማሕጸን የምትከፍት: ዕፀዋትንም ከባሕርያቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ:: እውነትም ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ስትል አለቀሰች::

ቅዱስ ኢያቄምም ወደ ተራራ ወጥቶ ለ፵ ቀናት አለቀሰ: ተማለለ:: ይህ ሲሆን ፪ቱም አርጅተው ነበር:: ሐምሌ ፴ ቀን ግን ነጭ ርግብ ፯ቱን ሰማያት ሰንጥቃ በማሕጸነ ሐና ስታድር አዩ:: ደስ ብሏቸው ለ፯ ቀናት ሱባኤ ይዘው ቅድስት ሐና እመቤታችንን ነሐሴ ፯ ቀን ጸነሰቻት::

ይሕም ለእነርሱም: ለወገኖቻቸውም ታላቅ ተድላ ሆነ:: ብጽዕት ሐና ግን ፈጣሪዋን ታከብረው ዘንድ በጐነትንና ንጽሕናን አበዛች:: ጸንሳ ሳለም ዕውራንን አበራች: ድውያንን ፈወሰች::

የጦሊቅ ልጅ በሞተ ጊዜም እያለቀሰች ስትዞረው ጥላዋ ቢያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነስቶ :- "ሰላም ለኪ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ" ብሎ ድንግል ማርያምን::
"ወሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ" ብሎ ቅድስት ሐናን አመስግኗል:: ትርጉሙም ድንግልን "የፀሐየ ጽድቅ እናቱ": ሐናን "ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አያቱ" ማለት ነው::

ይህንን ያዩ አይሁድ ቅድስት ሐናን ሊገድሉ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል:: ግን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አልፈቀደላቸውም:: ግንቦት ፩ ቀንም የሰማይና የምድር ንግስትን ሊባኖስ ተራራ ላይ ወልዳ ሽሙጥን ከሁላችንም አራቀች::

ስሟን "ማርያም-የአምላክ ስጦታ" ብለው ሰይመው ለ፫ ዓመታት አሳድገዋታል:: የሚገርመው በ፫ቱ ዓመታት ውስጥ ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር:: አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች:: ሁዋላ ግን መልሰውላታል::

ሌላኛው የሚደንቀው እግዚአብሔር የዓለም ውዱን ስጦታ እመ ብርሃንን ሰጣቸው:: እነርሱም ይሕችን ውድ ስጦታ ሳይሰስቱ ለፈጣሪ መለሱለት::

ቅድስት ሐና ድንግል ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በሁዋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለ፭ ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት: ትስማት ነበር:: እመቤታችን ፰ ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ::

ከክርስቶስ ልደት ፰ ዓመታት አስቀድማ ብጽዕት እናት ሐና በዚህች ቀን ዐረፈች:: ትንሽ ቆይቶም ባለቤቷ ቅዱስ ኢያቄም ተከተላት እኛም ልጆቿ "ብጽዕት ሐና ብጽዓን ይገባሻል!" እያልን እናመስግናት::

ሊቃውንቱ ለእርሷ እንዲህ ብለዋልና :-

"ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኩሉ ምዕራጋ::
ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ::
ሐና ብጽዕት ተፈስሒ እንበለ ንትጋ::
እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ::
እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ::" አርኬ

አምላከ ብጽዕት ሐና በምልጃዋ ከዘለዓለም እሳት ያድነን:: ጸጋ በረከቷንም ይክፈለን::

@ortodoxmezmur