Get Mystery Box with random crypto!

​​እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኳን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በሁዋላ ተሰይፏል:: ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ::

ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ "የሰማዕታት አለቃቸው" : "ፀሐይና የንጋት ኮከብ" በሚል ይጠራል::

"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ::
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ::" እንዲል መጽሐፍ::

ከ7 ዓመታት መከራ በሁዋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም ወርደውለታል::

ይህቺ ዕለት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ቅዳሴ ቤቱ ናት:: እርሱ በ390ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂጥ ዓመታት በሁዋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው: አጽሙን አፍልሠው በዚህች ቀን ቀድሰዋታል::

ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በሁዋላ ተአምረኛ ነውና አንዷን እንመልከት:: በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የ47 ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ::

በ305 ዓ/ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ:: የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ላይ ተሳለቀ::

ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው:: እንደ እብድ ሆኖ ሞተ:: ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ:: ይሕን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ:: ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዐይኑን አጠፉት::

እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት:: ራሱን ቢመታው ደነዘዘ:: የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለ7 ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮ ሰይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል::

አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት: ከበረከቱም ይክፈለን::

@ortodoxmezmur