Get Mystery Box with random crypto!

​​ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጸሐፊ  ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጸሐፊ  ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒሌ  ጋር በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ጉደይ ውይይት አደረጉ።

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኀን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ጥር ፳፭  ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ጄኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ በሚገኘው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በመገኘት ከዋና ጸሐፊው ቄስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጄሪ ፒሌ ጋር ውይይት አደረጉ። 

ብፁዕነታቸው  ዋና ጸሐፊው በቅርቡ ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት በመመረጣቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ስም የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል።

ቤተ ክርስቲያን የምክር ቤቱ መስራችና ንቁ አባል በመሆን የበኩልዋን ሚና እየተወጣች መሆኑን አስታውሰው ይህ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማትን ወቅታዊ ሁኔታ ያብራሩላቸው ሲሆን የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና እና ሕግጋት የጣሱ ጥቂት አፈንጋጭ አካላት ድርጊታቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕልውና ላይ የሚያስከትለውን ታላቅ አደጋ በመገንዘብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወገዙና የተለዩ ቢሆንም መንግሥት የሕግ የበላይነትንና የሕዝብን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ሐዘንና ጭንቀት ፈጥሯል።

በዚህም ጳጳሳት እየተሳደዱ፣ ካህናት እየታሰሩ፣ ምዕመናን እየተደበደቡ ይገኛሉ። እንዲህም ሆኖ ሕግ የጣሱት አካላት በንስሐና በይቅርታ ቢመለሱ ቤተ ክርስቲያን በሯን ክፍት አድርጋ እየጠበቀች ትገኛለች። ምክር ቤቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ተቋማዊ ልዕልና፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰላምና ለፍትሕ አጋርነቱን እንዲገልጽ ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል።

ዋና ጸሐፊው  ለተደረገላችው ዝርዝር ማብራሪያ አመስግነው ይህች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ የገጠማት ፈተና በእጅጉ አንደሚያሳስባቸውና ጉዳዩን በቅርበት መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በብፁዕነታቸው በኩል ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  ሰላምታና መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።  ከብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ጋር መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ሃይለ ጊዮርጊስ በስዊትዘርላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የጄኔቫ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ አመራር ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ተከትሎ ዋና ጸሐፊው በማግስቱ አጋርነታቸውን የሚያሳይ መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሐዋርያት የተመሰረተች፣ ሁልጊዜም ለአንድነትና ለሰላም የደም መስዋዕትነትም ጭምር ስትከፍል የኖረች ናት ብለዋል። አዲስ ሲኖዶስ ለመመስረት በሚደረገው ሙከራ ማዘናቸውን ገልጸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠበቅ በጸሎት እግዚአብሔርን ጠይቀዋል። የሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይላት ሁሉ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይዋን በአላት መንፈሳዊ ቀኖና እና ሕግ ለመፍታት ብሎም የምዕመኗን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ: ኢኦተቤ ቴቪ