Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን አደረሳችሁ ††† እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰ | "ቤተ ማርያም መንፈሳዊ ሚዲያ💒

እንኳን አደረሳችሁ
††† እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ኤርምያስ †††

††† ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው:: አባቱ ኬልቅዩ ይባላል:: ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር::

እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ: ቀድሼሃለሁ" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል:: (ኤር. 1:5)

ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም:: ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" (ባለ እንባው ነቢይ) ይሉታል::

ዘመኑ ዘመነ-ኃጢአት (ዘመነ ዐጸባ) ነበር:: እሥራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም:: ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት:: እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው::

የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በ722 አሦር (ነነዌ) አወረዳቸው:: በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ:: ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ::

ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው:: ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ: እኩሉንም ማርኮ: ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ: የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በ586 ባቢሎን አወረዳቸው::

ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን (ከመከራው የተረፉት) ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም::
በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት : ነቢይ : መምሕርም ነውና ወደ ሕዝቡ (ወደ ባቢሎን) ወረደ:: በዚያም ትንቢትን እየተናገረ : ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሐገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል:: ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል::

ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እሥራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው::

በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት : ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ) አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ:: አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል:: ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው:: ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት::

ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል / ጽፏል:: ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ : በመጽሐፈ ባሮክ : በገድለ ኤርምያስ : በዜና ብጹዐን : በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል::

††† ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን::

††† ግንቦት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ (ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

††† "ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል : ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር : ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም:: እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል:: እላችሁአለሁና : በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም::"
(ማቴ. ፳፫፥፴፯-፴፱)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

https://t.me/zikirekdusn
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!

ዝክረቅዱሳን (ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት)

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/zikirekdusn