Get Mystery Box with random crypto!

የገና ጾም /ጾመ ነቢያት/ የገና ጾም ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት | የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ገፅ

የገና ጾም /ጾመ ነቢያት/
የገና ጾም ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ ነቢያት ጌተችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዚህ ዓለም መጥቶ በሥጋ የታመሙትን በተአምራት፣ በነፍስ የታመሙትን ደግሞ በትምህርት ማዳኑን፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ መቀበሉንና መሰቀሉን፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑት እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳ የትንቢቱን ፍጸሜ በዘመናቸው ባያዩትም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ ነቢያት በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ አባቶቻችንም ይህን መሠረት ባደረገ መልኩ በጾመ ነቢያት ውስጥ ያሉ ጊዜያትን በመከፋፈል ዘመነ ስብከት፣ብርሃን፣ኖላዊ በማለት ትምህርት እንድንማርባቸው አድርገው አዘጋጅተውልናል።
ዘመነ ስብከት
ከነቢያት መካከል እነ ኢሳይያስ የነቢያት ጾም እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋል። ኢሳ 58-1፡፡ በዘመነ ሐዲስም ነቢያት አስቀድመው ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለትንና ሱባዔ የቆጠሩለትን ሐዋርያት ያላቸውን ትተው ተከተሉት ፈቃዱንም ፈጸሙ፡፡ ስለዚህ ምእመናን ክፉ ሐሳባቸውን አርቀው ርኵሰትን አስወግደው ፍጹም ለእግዚአብሔር እንዲገዙ በዚህ የጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይሰጣል፣ ስብከት ይሰበካል። የሚነበበውም ምንባብ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን የሰበኩበት፣ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበትና የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡
ብርሃን
ክቡር ዳዊት «አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42-3/ እያለ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ወገን እንዲወለድ ትንቢት ስለተናገረ ይህ የሚታሰብበት ነው፡፡ ነቢዩ ዓለም በጨለማ ስለሆነች ብርሃንህን ላክ፣ ሐሰትና የሐሰት አባት ነግሦባታልና እውነትህን ላክ አለ፡፡ ወልድን ላክልን ማለቱ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ዮሐንስ «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» ብሎ ሲመሰክር ጌታም ራሱ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም» ብሎ ተናግሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 8-12 እንዲሁም ብርሃንን እውነት ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ላክልን ሲል ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ስደድልን ማለቱ ነው፡፡
ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጣን፣ ማለቱ ደግሞ ንስሐ ከመግባት ቸል እንዳይሉ ይነግራቸዋል፡፡ ነቢያት የጥል ግድግዳን ሰብሮ መለያየትን አጥፍቶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣቸውን ሽተው ውረድ ተወለድ አድነንም እያሉ ጮኹ፣ እውነተኛ ብርሃን ጌታችን ጊዜው ሲደርስ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ በመምጣቱም በጨለማ ያለው በብርሃን እንዲገለጥ ለሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚያውቁባት ዕውቀት ተሰጠች፡፡
ኖላዊ
ኖላዊ ተብሎ የሚጠራው ከብርሃን ቀጥሎ ያለው ሳምንት ነው፡፡ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡ ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡
ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ቃል ይፈጸም ዘንድ የሰው ልጆችም ድኅነት ማረጋገጫ እውን ይሆን ዘንድ እንደ ጾሙ እንደ ጸለዩ እኛም እንደ አባቶቻችን እንደ ነቢያት በፍቅር፣ በጾም በጸሎት ዛሬም እናስበዋለን፡፡ ነቢያት በረከት እንዳገኙ እኛም ከእግዚአብሔር በረከት እናገኛለን፡፡ ለዚህም አምላካችን ይርዳን አሜን፡፡