Get Mystery Box with random crypto!

'እግዚአብሄር ይቅርታ አድራጊ ነው' መዝ 103፥6 የእውነት እግዚአብሄር ይቅርታ አድራጊ ነው። ይ | የእግዚአብሔር ፀጋ- THE GRACE OF GOD👑

"እግዚአብሄር ይቅርታ አድራጊ ነው" መዝ 103፥6

የእውነት እግዚአብሄር ይቅርታ አድራጊ ነው። ይቅርታም ሲያደርግ አመንትቶ አይደለም ከባህሪው ነው። ሰው ይቅርታ የሚለው በደልን ደብቆ ይዞ ነው፤ ደግመን ስንቀያየም ከዚህ በፊትም እንዲህ አርገኸኝ ነበር ይላል እግዚአብሄር ግን ደግመን እንደምንበድለው እንደምናስቀይመው እያወቀ ይቅር ይለናል።እርሱ ብዙ እድል ይሰጠናል ሰው ግን የመጨረሻ እድል ይሰጠናል ከዚህ በኃላ ይህ የመጨረሻ እድልህ ነው ይላል እግዚአብሄር ግን ብዙ እድል ይሰጠናል። የመጨረሻ እድል የማይሰጥ ሁሌም የይቅርታ ልብ ያለው አባት ስሙ ይባረክ። ጴጥሮስን አስቡት ሽምጥጥ አርጎ እየካደ ይቅርታን ያገኘ ዳግመኛ እድልን ያገኘ ሰው ነው። ብዙ መገለጥና መገልበጥ በህይወቱ ያየው ጴጥሮስ አንተ ከሀዲ ነህ ሳይለው ግልገል ጠቦት ለማሰማራትም እረኛ አደረገው። በትላንት ስህተታችን ሳይሆን ነገን አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ጉዞን የሚያስጀምር ጌታ ነው።ይቅርታ የሚጠይቀው ሰው የበደለው ብቻ አይደለም።በአለም ስርዓት በዳይ ይቅርታ ይጠይቅ ይሆናል በክርስትና ግን ተበድሎም ይቅርታ ይላል።ትክክል
ብትሆንም ይቅርታ መጠየቅ ወሳኝ ነገር ነው።ይቅርታ መጠየቅ ያለብህ የተሳሳተ ነገር በማድረግህ ሳይሆን የተሳሳተ ስሜት በመፍጠርህ ነው እርሱም ቅሬታ ነው።ትክክል ሆነህ የተሳሳተ ስሜት ከፈጠርክ የሚስተካከለው በይቅርታ ሀይል ነው።ትክክል ብትሆንም ይቅርታ የመጠየቅ ግዴታ ያለብህ ክርስቲያን ስለሆንክ ነው ሲቀጥልም ቅሬታው አንተ የፈጠርከው የተሳሳተ ስሜት በመሆኑ ነው።ስለዚህ ይቅርታ የምትጠይቀው ስለተሳሳትክ ሳይሆን ትክክል ብትሆንም ለቅሬታው መፈጠር የአንተ አስተዋፅኦ የመኖሩን ያህል ቅሬታውን ለማጥፋትም የአንተ አስተዋፅኦ መኖር ስላለበት ነው። "በምድር ላይ መድሀኒት የታጣላቸው በሽታዎች የሚፈወሱት በይቅርታ ነው"።
እስቲ ሁለት በጣም የሚዋደዱ ፍቅረኛሞችን አስቡ እነዚህ ሁለት ፍቅረኛሞች የሚዋደዱት መሀላቸው ግጭት ስለማይፈጠር ወይም ስለማይጣሉ አይደለም ይቅርታ ስለሚባባሉ ነው።የተጎዳው ፍቅር የሚስተካከለው በይቅርታ ሀይል ስሜት ሲጠገን ነው።የጉዋደኛ ልብ የስሜት ሸራ ነው።ስትፈልግ ፍቅርን ሳትፈልግ ጥላቻን ትስልበታለህ።ጥላቻ ስእል ሳይሆን የልብ መጎዳት ነው።ፍቅር ግን ልብን የሚያሳምር ያማረ ስዕል ነው።ስዕሉ የሚደበዝዘው በቆሸሸ ብሩሽ ተነካክቶ በቅሬታ ስሜት ፍቅር ሲደበዝዝ ነው።ቅሬታ ማለት ፍቅር ተበላሽቶ የሚፈጠር የተሳሳተ ስሜት ነው።ቅሬታውን ወደ ፍቅር ለመመለስ የሚቻለው በይቅርታ ላጲስ የተሳሳተውን ስሜት ማጥፋት ሲቻል ነው።ቅሬታ ልብ ላይ ለመቆየት የራሱ አቅም የለውም።ቅሬታ የተሳሳተ ስሜት ሆኖ ልብ ላይ የሚቆየው በይቅርታ ላጲስ ጠፍቶ በፍቅር እስኪተካ እንዲሁም ልብ በጥላቻ ተጎድቶ ቅሬታን መሸከም የማይችልበት ደረጃ እስኪደርስ ነው። ይቅርታ የአራት ፊደሎች ጉዳይ ብቻ አይደለም። ያቆሰልነውን ልብ የምናክምበት ለቁስሉ የፈውስ ዘይት የሚሆን አካል ያለው ቃል ነው።እስቲ ልባችሁ ይቅርታ ያላደረገላቸውን ውስጣችሁ የሚርመሰመሱትን ሰዎች አስቡ ለነዚህ ሰዎች ዛሬ የይቅርታ መድረክ ዘርጉላቸው ይቅርታ አድርጉላቸው በእውነት ትታደሳላችሁ ውስጣችሁ ያርፋል ሰላም ያገኛል።መፅሀፍ በ 1ኛ ቆሮ 2፥16 ላይ "እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን" ይላል ታዲያ የክርስቶስ ልብ ምን አይነት ነው ይቅርታ አድራጊ ነው ያውም እየሞተ ይቅርታ የሚለምን ነው። ይቅርታ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ የክርስቶስ ልብ የለንም ምክንያቱም የክርስቶስ ልብ ከፊል ደመናማ አይደለም ምሉዕ ብርሀን እንጂ።
የይቅርታ ቀን ይሁንልን



መልካም ቀን!!




ጌታ ኢየሱስ ይመጣል!!!



https://t.me/One_way_He