Get Mystery Box with random crypto!

ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው አለ ነቢዩ ።፦ የዕለት ጥዝጣዜ አልብን ፦ እርሱም ቁስል ይባላል ። | Nolawi ኖላዊ ኄር

ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው አለ ነቢዩ ።፦ የዕለት ጥዝጣዜ አልብን ፦ እርሱም ቁስል ይባላል ። በዕለቱ የሚሰማን ችግር አለ ። የሰላም ባጀት በመንግሥታት አቋም ዕቅድ ተለቆ አያውቅም አይለቀቅምም ። የሰላምን ባጀት ያለ ገደብ የሚለቅ የሰላም አለቃ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ከዕለቱ ጋር የሚለቀቅልን የሰላም ባጀት ከጸባዖቶ ተቋርጦ አያውቅም ። ውኃ ልማት እሰከ ቤታችን ውኃ ይለቃል ። ቦኖውን ከፍቶት መጠቀም ግን የባለቤቱ ድርሻ ነው ። ክርስቶስ ወደ ልባችን ፣ ወደ ቤታችን ፣ ወደ መንደራችን ፣ ወደ ከተማችን ፣ ወደ  ሀገራችን የሚለቀውን የሰላም በረከት ልብን ለንስሐ ከፍቶ  ፣ ኑሮን ለቃሉ አዘጋጀቶ ፣ ውሎን ለምክሩ ለቅቆ መገኘት ያስፈልጋል ። ያለዚያ የዕለት ችግሮቻችንን እንኳን እንደ ሀገር እንደ መንደርም መቅዘፍ ይከብደናል ። ለዚህ ነው ነብዩ የዕለት ችግሮቻችንን በቁስል የመሰለው ። ቁስል ይጠዘጥዛል ። አትንኩኝ ባይነትን ያለማምዳል ። ዛሬ የእኛ ቁስል ዘር ነው ። መርጠን ባልተወለድንበት ዘር መርጠን መታመማችን የሚያሳዝን ነው ። አማራ ተንክቶ ሀድያ ካልደማ ፥ ሀድያ ደምቶ ኦሮሞ ከላከመ ፥ ትግሬ ተርቦ ጉራጌ ካልመገበ እያልን ጨፍረን ሰው ግን ሰው መሆኑ ገና አልገባንም ። በተወለደበት አከባቢ  በወጣለት የብሔር ስም ሰው አይመዘንም ሰው ሰው ነው የሚል ትምክህት ያስፈልጋል ። ዛሬ የእኛ ትምክህት አማረነቴ ኩራቴ ፣ ኦሮሞነቴ ብርታቴ ትግሬነቴ ክብሬ የሚል ነው ። የጋራ አንድነት እንጂ የጋራ ዘር ሀገርን አያሻግርም ። ቢመኩበት የማይጥም ትምክህት ይዘን ለጨነገፍ ፅንስ ልደት አክብረናል እግዚአብሔር በንጹሕ መዳፉ የኢትዮጵያን ቁስል ይዳባስ !

ለዘመናት የተጠራቀመ ችግር አለብን ። ነብዩ ይህን በእበጥ መስሎታል ። በመቶ ዓመት ታሩክ ዛሬ ከሚጣላ ሕዝብ በላይ ምን የሚያሳፍር ሕዝብ አለ ?! ይህን ትምህርት ቤት እገሌ የሚበል መንግሥት ነው ያሰራው ተብሎ ከድንጋይ ጋር ከሚጣላ ሕዝብ በላይ ምን የሚያሳፍር ሕዝብ አለ ?! ሰው ከድንጋይ ጋር ይጣላል ?! እገሌ የሚባል ዘማሪ ከቤተክርስቲያን ተውግዟል ሲባል መዝሙሩን ተጸይፎ ሲዲውን ከሚያቃጥል ሕዝብ በላይ ምን የሚያሳፍር ሕዝብ አለ ? ሰው ከመዝሙር ጋር ይጣላል ?!  ወገኖቼ ቂመኛ ሕዝብ አይድንም ። ክርስቶስ በማዋል ሥጋዌው ያስተማረን ብዙ ትእዛዛት ቢኖሩ እንኳ ከትእዛዛት የሚበልጠው ትእዛዝ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚል ነው ። ሰው እግዚአብሔርን እቢ ካለ የማይሆነው የለምና የእኛ ጉድ ገደብ የለውም ። እንኳን የዛሬ ጠላታችንን መውደድ አይደለም የመቶ ዓመት አፅም ጋር ቂም ያለን ሰዎች ነን ። እረ እግዚአብሔር ያስበን ! የሕይወት መጽሐፍ እንዲህ ይላል ፦ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። (ማቴ 5:43-48 ) ። ቃሉን ስትመረምሩ ጌታ እየተናገረ ያለው አንድ ነገር ነው ። ጠላቶቻችሁን ለመውደድ ወዳጆቻችሁን በመውደድ ጀምሩ የሚል ነው ። እኛ በሚያሳዝን መልኩ የዛሬውን ጠላት አይደለም ለመውደድ ለማወቅም ዝግጁ አይደለንም ። ምክንያቱም እኛ በመቶ ዓመት የጠላት ተሪክ ላይ ነው ያለነው ። ፈትሉ የረዘመ የቂም ትብታብ ውስጥ ነን ወገኖቼ አረ እኛንስ እግዚአብሔር ያስበን ! ። አንደ ሰውነት ሰለ ሀገሬ ኢትዮጵያ አዝናለሁ ። እንደ መንፈሳዊነት ግን ተስፋ አደርጋለሁ ። እግዚአብሔር ይህችን የዘመን ቂም ያጨለማት ሀገር በብርሃን ዓምዱ ከውድቀት ይመልሳት !


የሚመግልም ነው አለ ነቢዩ፦ ሽታው የሚያውክ መግል አለብን ። ለዓለም ዜና ርዕስ የሚሆን የግድያ ፣ የግፍ ግፍ ፣ የጥላቻ ልክ ፣ የነውር ካባ ፣ የውርደት ልክ አለብን ። ብክብራችን በምንታወቅበት ዓለም በነውራችን ፣ በፍቅር በምንታወቅበት ዓለም በጥላቻ ፣ በመረዳዳት በምንታወቅበት ዓለም በገዳደል እየታወቅን ነውና ወዮውልን ። ዓለምስ ቢያውቅ ለማለት ነው እግዚአብሔር እያወቀ ዝም ካለን ግን ጉዳዩ አስጊ ነው ። ''አንዲት ሴት ያሉት ነገር ሁሌ ያስደንግጠኛል ። እንዲህ አሉ እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ካልቀጣን ሰዶምና ጎመራን ይቅርታ መጠየቅ አለበት" አዎ ቅጣት ያንስብናል ። ግን እግዚአብሔር ተመግሶናል ። እግዚአብሔር የሚናገርበት ዘመን  የምሕረት ዘመን ነው ። እግዚአብሔር ዝም የሚልበት ዘመን አስፈሪ ዘመን ነው ። በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ ነው ነገሩ ። በእግዚአብሔር ምሕረት ቆመን ማቄም ፣ በእግዚአብሔር ይቅርታ ኖረን መግደል ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት ቆመን መበቃቀል የሚያሳዝን ነው ። ችግሩ ገድሎ የሙት ልጅ አይኮንምና መግሉ ለሚሸት ለዚህ ውድቀት ዋና ተባባሪ ነን ። ወገኖቼ ስትሆኑም አለመሆንን ተቀበሉ እንጂ ! ። እንዴ የሆነ መንደር ውስጥ 20 ዓመት ተኑሮወ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ነውር ነው ። እርሱ ለመታወቂያ በቂ ነው ። አረ ኢትዮጵያን ኑሩላትና ፣ ውደዷትና ፣ ስሩላትና ፣ ጥቅሟትና ኢትዮጵያዊ ነኝ በሉ ። እስከመቼ በመታወቂያ ወረቀት ይፎከራል ? አረ ተዉ ይህ አያሻግረንም ። እኛ የተውናትን ሀገር ሌለኛው ወገን አይደለም እግዚአብሔር እንኳ አይደግፋትም ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ጥሎ አይጥልም የሚሉ አዝማሪዎች አሉን ። አረ ተዉ እግዚአብሔር እስራኤልንም ጥሏል ። እንደ እስራኤል የተመረጠ እንደ እስራኤል የወደቀ የለም ። ከድንጋይ እና ከመዝሙር ጋር የሚጣላ ሕዝብ አይወድቅም ማለት ዘበት ነው ። ውድቀት ስብራት ቢኖረውም እንዲጠገን አድርጎ መሰበርም ግን ያስፈልጋል ። ከመቶ ዓመት ታሪክ ላይ ዛሬ የሚያቄም ትውልድ ነጌን መድረሱ ያሰጋል ። በማንማርበት ትናንት ውስጥ ዛሬን መቆም ፣ በማንመለስበት ዛሬ ውስጥ ነጌን መድረስ አንችልም ። ትናንት ስህተት ቢኖረው ለዛሬ እንዲታረም ነው ። ዛሬ ውድቀት ቢኖረው ነጌ እንዲነሳ ነው ። አረ መግላችን ያጸይፋል ሽተው ምድር አውኳል እናስተውል ! እግዚአብሔር በፍቅሩ መዓዛ የነውር መግል ያሸተታትን ኢትዮጵያ ይመልሳት ።

አልፈረጠም አለ ነቢዩ ፦ ማለትም አልተወያየንም ። ችግሩ ምንድነው ብሎ የሚጠይቅ የለም ። በፈጠራ ታሪክ ነው የምንጣላው ። ያሰብነው እንደሆነ አድርገን ነው የምንባለው እያለ ነው ነቢዩ ። ችግር ከወራጁ አይገደብም ። ቢገደብም የሚዘልቅ ሳይሆን የሚደጋገም ይሆናል ። ችግርን ከምንጩ ለመገደብ መወያየት ፣ መግባባት ፣ ሀሳብን  ማክበር  ያስፈልገናል ። አልያ አንድነቱ እስከ ወራጁ ይሆንና ችግሩ ይደጋገማል ። አንድነታችን እስከ ችግሩ ምንጭ ካልሆነ ችግርን መገላገልም ሆነ ማቆም አይቻልም ።