#ጋና
" የእኔን ጨምሮ የሁሉም ተሿሚዎች ደመወዝ በ30 በመቶ ቀንሷል " - የጋና ፕሬዜዳንት
የጋናው ፕሬዝደንት ናና አዶ ዳንኩዋ አኩፎ-አዶ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ የራሳቸውን ጨምሮ የሁሉም ተሿሚዎቻቸው ደመወዝ በ30 % እንዲቀንስ መደረጉን አስታውቀዋል።
ይህን ያስታወቁት ትላንትና የዒድ አል-አድሃ በዓል ሲከበር ባሰሙት ንግግር ነው።
የ30% ቅነሳው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን፣ የመንግስት ኤጀንሲዎችን እና መምሪያዎችን ወጪ ይነካልም ተብሏል።
ፕሬዜዳንቱ ፤ መንግስት እያሽቆለቆለ ያለውን ኢኮኖሚ ለመታደግ በሚያደርገው ጥረት ጋናውያን መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ተማጽነዋል።
" አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሁላችንም መስዋዕትነት መክፈል አለብን " ያሉት ፕሬዜዳንቱ " የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ መምሪያዎች እና ኤጀንሲዎች ወጪ በ30 በመቶ ቀንሷል። የእኔን ጨምሮ የሁሉም ተሿሚዎች ደመወዝም በ30 በመቶ ቀንሷል " ብለዋል።
የነዳጅ ኩፖን ምደባ በ50 % መቀነሱን እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች መታገዳቸውን ገልፀዋል።
ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የገለፁት ፕሬዜዳንቱ ጋናውያን እንዲታገሷቸው አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ናና አዶ አኩፎ አዶ እኤአ ሰኔ 1/2022 የገንዘብ ሚኒስትሩ ኬን ኦፎሪ-አታ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር ይፋዊ ግንኙነቶችን እንዲጀምሩ አዘው ነበር።
የIMF ድጋፍ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በቅርቡ የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ እያጋጠሙ ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ ነው ተብሏል።
ምንጭ - ቲክቫህ