Get Mystery Box with random crypto!

ሌባው የመስጂድ ኢማም ባልና ሚስት ከረመዷን ወራት ባንዱ በሰፈራቸው የሚገኙ | ሙሀመድዬዬዬ🤩😘😍🤩

ሌባው የመስጂድ ኢማም


ባልና ሚስት ከረመዷን ወራት ባንዱ በሰፈራቸው የሚገኙትን ታዋቂ የመስጂድ ኢማም ለፊጥራ ጋበዟቸው። ኢማሙም ግብዣውን በክብር ተቀበሉ። የቤቱ እማወራ የምግብ ማዕዱን ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ እያለች ሳለ ገንዘቧን ጠረጴዛው ላይ ጥላ ወደ ኩሽና አመራች። ፊጥራው ተጠናቀቀ። ኢማሙም ሄዱ። ሚስት ገንዘቧ እንደጠፋ አስተዋለች። «ገንዘቡን የሰረቀው ማን ነው?» ተብሎ አይጠየቅ ነገር ባልና ሚስት ልጆች የሏቸውም። በወቅቱ ወደቤት የመጡት የመስጂዱ ኢማም ብቻ ናቸው። ውስጧ በጥርጣሬ ተናጠ። ታሪኩን ለባለቤቷ አጫወተችው። የመስጂዱን ኢማም እንዲያማክራቸውና ጉዳዩን እንዲያረጋግጥ ጠየቀችው። «ኧረ ነውር ነው ፤ ባይሆን ከኢማሙ ጋር የፈጠርነውን ስር የሰደደ ግንኙነት አቋርጠን ፋይሉን እንዘጋለን እንጂ እንዲህ አይነት ጥያቄ ማንሳት የማይታሰብ ነው» በማለት መለሰላት።

ቀናት በንፋስ ፍጥነት ከነፉ። ቀጣዩ ረመዷን ገባ። ባል ከሚስቱ ጋር ተቀመጠ። «እንግዲህ የእዝነት እና የይቅርታ ወር ስለገባ ያለፈውን መርሳት አለብን። እንደምታውቂው ኢማሙም ቤተሰብ የላቸውም። የኛው ስለሆኑ ዘንድሮም ቢሆን ፊጥራ ልንጋብዛቸው ይገባል» በማለት ሚስቱን አማከራት። ሚስት ለአፍታ ዝም ካለች በኋላ «በሃሳብህ እስማማለሁ፤ ነገር ግን የማስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ ይኖራል። እርሱም የባለፈው ዓመት ረመዷን ላይ ስለተሰረቀው የገንዘብ ጉዳይ በግልጽ እንድታወሩ እፈልጋለሁ» አለችው። ባቀረበችው ሃሳብ ተስማማ።

የመስጂዱ ኢማም ግብዣውን ተቀብለው ከቤት መጡ። ፊጥራውን ከጨረሱ በኋላ የቤቱ አባወራ ጉዳዩን በይፋ አነሳው። ስለ ገንዘቡ ሁኔታ በቀጥታ ጠየቃቸው። ከፍተኛ የሀፍረት ስሜት ተሰማቸው። እንባቸው በጉንጮቻቸው ላይ ተንኳለለ። ካቀረቀሩበት ቀና አሉ። አይኖቻቸው የእንባ ቋጠሯቸውን እንደፈቱ ነው። ሚስት ፈጠን ብላ
« ኢማም ሆይ! ምን ሆነው ነው የሚያለቅሱት ?» በማለት ጠየቀቻቸው። «አዎ! ገንዘቡን ያነሳሁት እኔ ነኝ። ያስቀመጥኩትም የመጽሃፍት መደርደሪያው ላይ ከተቀመጠው ብቸኛ ቁርኣን ውስጥ ነው። እንባዬ የፈሰሰውም ረመዷንን ጨምሮ ለ 365 ቀናት ያህል የአላህን መጽሃፍ ገልጣችሁ አንድ ፊደል እንኳ ባለመቅራታችሁ ውስጤን ተሰምቶት ነው» በማለት ምላሽ ሰጡ። በዚህ ጊዜ የቤቱ አባወራ በፍጥነት መደርደሪያው ላይ ወደተቀመጠው ቁርኣን አመራ። ገንዘቡንም የቁርኣኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ምዕራፍ መሃል ላይ ተቀመጦ አገኘው። ሚስት እንባዋ ግድቡን ጥሶ ፈሰሰ። ኢማሙን በክፉ በመጠርጠሯም ይቅርታ ጠየቀቻቸው። «ልጄ ሆይ! እኔ ደካማ የአላህ ባሪያ ነኝ፤ ይልቅ አመቱን ሙሉ ቁርኣኑን ችላ በማለትሽ ይቅርታና ምህረት ከአላህ ጠይቂ» በማለት መከሯት።

እኛስ መቼ ይሆን ለመጨረሻ ጊዜ የአላህን ቃል ከፍተን ያነበብነው ? ነፍሳችንን ሳንዋሽ እውነቱን ለራሳችን እንገረው
ወገኖቼ የአላህ ቃል እየጠራን ቢሆንም ችላ ብለነዋል።
https://t.me/muhmedeye